በላሊበላ የተከበረው የገና በዓል የቱሪዝም ዘርፉን ለማነቃቃት አግዟል- የሰሜን ወሎ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ - ኢዜአ አማርኛ
በላሊበላ የተከበረው የገና በዓል የቱሪዝም ዘርፉን ለማነቃቃት አግዟል- የሰሜን ወሎ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ
ወልዲያ፤ ታህሳስ 29 / 2016(ኢዜአ) ፡- በላሊበላ የተከበረው የዘንድሮው የልደት በዓል ተቀዛቅዞ የነበረውን የቱሪዝም ዘርፉን ለማነቃቃት አግዟል ሲል የሰሜን ወሎ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ አስታወቀ።
የመምሪያው ኃላፊ አቶ ፀሐይነው ሲሳይ እንዳሉት፤ የዘንድሮው የልደት በዓል በደማቅ ስነ-ስርዓት በሰላም ተከብሯል።
የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኝዎች በአውሮፕላን፣ በተሽከርካሪና በእግር ተጓጉዘው በበዓሉ ላይ መታደማቸውን ገልጸዋል።
ያለፉት ሶስትና አራት ዓመታት በኮሮናና በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት በቱሪዝም እንቅስቃሴው ላይ ትልቅ ተፅዕኖ አሳድሮ መቆየቱን አስታውሰዋል።
ዘንድሮም ችግር ቢያገጥምም አሁን ባለው ሰላም 512 ሺህ 271 እንግዶች የልደት በዓልን በላሊበላ ተገኝተው ማክበራቸውን አስታውቀዋል።
በዚህ በዓል አከባበር 271 ከአውሮፓ፤ አሜሪካና ሩቅ ምስራቅ ሃገራት እንዲሁም ከሃገር ውስጥ ከተለያዩ ክልሎች የመጡ እንግዶች ታዳሚ መሆናቸውን አብራርተዋል።
ይህም ተቀዛቅዞ የቆየውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ በማነቃቃት መልካም አጋጣሚ መፍጠሩን ጠቅሰው፤ ከሀገር ውስጥና ከውጭ እንግዶችም ከ209 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተገኝቷል ብለዋል።
የልደት በዓልን በቅዱሱና ታሪካዊ ቦታ ላይ ማክበራችን ታላቅ መንፈሳዊ እርካታን ፈጥሮብኛል ያሉት ደግሞ ከባህር ዳር ከተማ በመምጣት በበዓሉ የታደሙት ወይዘሮ አብባ ኃይሉ ናቸው።
በበዓሉ ለመታደም ከሳምንት በፊት ላሊበላ መግባታቸውን ጠቅሰው፤ በቆይታዬ ከላሊበላ 40 ኪሎሜትር ርቀት የሚገኘውን "ይምርሃነ ክርስቶስን ጨምሮ በዙሪያ የሚገኙ ገዳማትን ጎብኝቼያለሁ " ብለዋል።
ዘንድሮ በተከበረው የልደት በዓልንና የቤዛኩሉ ስነ-ስርዓት መታደማቸውን ገልጸው፤ ስለ ውቅር አብያተ ክርስቲያናቱም ሆነ፣ ሰለ አከባበር ስነ-ስርዓቱ ካዩትና ከሰሙት በላይ እንደሆነባቸው ተናግረዋል።
ሌላዋ አስተያየታቸውን የሰጡን ከዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዝቋላ ወረዳ በእግር ተጉዞው በበዓሉ እንደታደሙ የገለጹት ደግሞ እማሆይ አገሪቱ ዋሴ ናቸው።
ክብረ-በዓሉን በሰላም በማክበራቸው መደሰታቸውን ጠቅሰው፤ ሰላማችን እንዲረጋገጥ ሁሉም የድርሻው ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
የውጭና የሃገር ውስጥ ጎብኝዎች በተገኙበት በላሊበላ የተከበረው የልደት በዓል በሰላም መጠናቀቁ ተመላክቷል።
በሰሜን ወሎ ዞን የሚገኘው የቅዱስ ላሊበላ ዉቅር አብያተ ክርስቲያናት በተባበሩት መንግስታት የትምህርት ፣የሳይንስና የባህል ድርጅት /ዩኔስኮ/በዓለም ቅርስነት ከተመዘገቡ የኢትዮጵያ ሀብቶች መካከል ተጠቃሽ ነው።