ቀጥታ፡

በስድስት ወራት በዲጂታል አማራጮች የ2 ነጥብ 8 ትሪሊየን ብር ግብይት ተፈፀመ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 29/2016(ኢዜአ)፦ በተያዘው በጀት አመት ስድስት ወራት በዲጂታል አማራጮች የ2 ነጥብ8  ትሪሊየን ብር ግብይት መፈጸሙን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስታወቀ።

የዲጂታል ባንኪንግ ደንበኞች ጥሬ ገንዘብ እንቅስቃሴ ሳይኖር በእጅ ስልክና በካርድ አማካኝነት አገልግሎት የሚያገኙበት ስርዓት መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጂታል ባንኪንግ ዲቪዥን የመርቸንትና የኤጀንት ማኔጅመንት ዳይሬክተር አቶ ብሌን ኃይለሚካኤል በበጀት ዓመቱ ስደስት ወራት የዲጅታል ግብይት እንቅስቃሴውን በተመለከተ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል። 

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሁን ላይ ከ12 ሚሊየን በላይ የኤ.ቲ.ኤምካርድ ተጠቃሚዎች፣ ከ9 ሚሊየን በላይ የሞባይል ባንኪንግና  ከ20 ሚሊየን በላይ ሲቢኢ ብር ተጠቃሚ ደንበኞች እንዳሉት ገልፀዋል።

የዲጂታል አማራጮችን የሚጠቀሙ የባንኩ ደንበኞች ቁጥር በየዓመቱ ከፍተኛ እድገት እያሳየ መሆኑንም ተናግረዋል።

በተያዘው በጀት አመት ስድስት ወራት ከ494 ሚሊየን በላይ ግብይቶች በዲጂታል አማራጮች ተከናውነው የ2 ነጥብ 8 ትሪሊየን ብር ግብይት መፈፀሙን ተናግረዋል።   

የዘንድሮው በጀት ዓመት ግብይት ከአምናው ተመሳሳይ ውቅት ጋር ሲነፃፀር በግብይት የ35 በመቶ እንዲሁም በገንዘብ መጠን የ118 በመቶ እድገት ማሳየቱን ገልጸዋል።  

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በቅርቡ አዳዲስ የዲጅታል አገልግሎቶችን ለደንበኞቹ ለማቅረበ መዘጋጀቱንም ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።    

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም