የመሰረተ ልማት ግንባታዎች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ አድርገው እንዲገነቡ እየሰራ መሆኑን ፌዴሬሽኑ አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
የመሰረተ ልማት ግንባታዎች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ አድርገው እንዲገነቡ እየሰራ መሆኑን ፌዴሬሽኑ አስታወቀ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 29/2016(ኢዜአ)፦በሀገሪቱ የሚከናወኑ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ አድርገው እንዲገነቡ ከሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ጋር በመቀናጀት እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌደሬሽን አስታውቋል።
በኢትዮጵያ ለአካል ጉዳተኞች የሚመጥን የመሠረተ ልማት ግንባታ አለመኖር በርካቶችን ለከፍተኛ እንግልት እና የጤና ችግር እንደዳረጋቸው ይነገራል።
የመንገድ ላይ የቁም እና የወለል ምልክቶች አለመኖር ፤ሕንጻዎች ለአካል ጉዳተኞች ምቹ አለመሆን፤ ተመጣጣኝ የመጸዳጃ አገልግሎቶች አለመኖር ከሚጠቀሱ ችግሮች መካከል ይካተታሉ፡፡
የመጓጓዣ አገልግሎቶች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ አለማድረጋቸው ችግሮቹን የሚያባብሱ ተጨማሪ ምክንያቶች መሆናቸውንም የአካል ጉዳተኞች በተደጋጋሚ ጊዜያት በምሬት ሲናገሩ ይደመጣል።
እንደ ሀገር የሚገነቡ በርካታ መሰረተ ልማቶች አካል ጉዳተኛውን የማህበረሰብ ክፍል ተጠቃሚ ከማድረግ አንጻር ከፍተቶች የሚስተዋልባቸው እንደሆኑም ሲገልጹ ይሰማል።
ይህንንም ችግር ለመፍታት የሚከናወኑ ተግባራትን በተመለከተ ኢዜአ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን እና የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣንን አነጋግሯል።
የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አባይነህ ጉጆ በሀገሪቱ የሚገነቡ በርካታ መሰረተ ልማቶች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ አድርገው እንደማይሰሩ ይናገራሉ፡፡
መሰረተ ልማቶች ከመገንባታቸው በፊት አካል ጉዳተኛውን ታሳቢ ያደረገ ንድፍ ከማዘጋጀት አንፃር የሚመለከታቸው ተቋማት በትኩረት ሊሰሩበት ይገባል ብለዋል።
ከህንጻ መሰረተ ልማት ምቹ አለመሆን ጋር ተያይዞ አካል ጉዳተኞች የሚያነሷቸውን ችግሮች ለመቅረፍ ፌዴሬሽኑ ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን ጋር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በተጨማሪም በአዲስ አበባ የሚሰሩ የአዳዲስ መንገዶች ግንባታና የነባር መንገዶች እድሳት በሚከናወኑበት ወቅት ለአካል ጉዳተኛው ምቹ እንዲሆኑ ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ጋርም እየሰሩ መሆኑን አክለዋል።
የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ እያሱ ሰለሞን በበኩላቸው በመዲናዋ በርካታ የመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታዎች እንደሚከናወኑ ተናግረዋል።
በአሁኑ ሰዓት የመንገድ መሰረተ ልማቶች አካል ጉዳተኛውን የማህበረሰብ ክፍል ታሳቢ ባደረጉ መልኩ እንዲገነቡ የሚያስችሉ ተግባራት በማከናወን ላይ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።