የቡና ጥራትና ምርታማነትን ለማሻሻል ለአርሶ አደሮች እየተሰጠ ያለው ስልጠና ውጤት እያመጣ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የቡና ጥራትና ምርታማነትን ለማሻሻል ለአርሶ አደሮች እየተሰጠ ያለው ስልጠና ውጤት እያመጣ ነው
አዲስ አበባ፤ታህሳስ 29/2016(ኢዜአ)፦ የቡና ጥራትና ምርታማነትን ለማሻሻል ለአርሶ አደሮች እየተሰጠ ያለው የመስክ ስልጠና ውጤት እያመጣ መሆኑን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ገለጸ።
የቡና ጥራትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን በተመለከተ ኢዜአ ከባለስልጣኑ የቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍቃዱ አደፍርስ ጋር ቆይታ አድርጓል።
በማብራሪያቸውም የቡና ምርታማነትንና ጥራትን ለማሳደግ ባለፉት ዓመታት የተለያዩ ተግባራት ሲከናወኑ መቆየቱን ገልጸው የምርቱን ብዛትና ጥራት ማሳደግ ተችሏል ብለዋል።
በዚህም ቀደም ሲል በሄክታር በአማካይ ስድስት ኩንታል የነበረው ምርታማነት አሁን ላይ ወደ 7 ነጥብ 5 ማደጉን ገልጸዋል።
በቀጣይ አራት አመት ደግሞ በሄክታር 12 ኩንታልና የጥራት ደረጃንም ወደ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ለማድረስ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በቡና ልማት አሲዳማ መሬትን የማከም፣ የበሽታ መከላከል፣ የግብዓት አጠቃቀምን የማሻሻልና ሌሎችም ስራዎች በሳይንሳዊ መልኩ እየተከናወኑ መሆኑን አብራርተዋል።
የኤክስቴንሽን አሰራርን የማጠናከር ስራም ከባለድርሻ አካላት ጋር ፕሮጀክት ተቀርጾ እየተከናወነ ይገኛል ነው ያሉት።
የቡና ጥራትና ምርታማነትን ለማሻሻል ለአርሶ አደሮች እየተሰጠ ያለው የመስክ ስልጠና ውጤት እያመጣ መሆኑን የጠቀሱት ዋና ስራ አስፈጻሚው እስካሁን በስድስት ቡና አብቃይ ክልሎች ከኢዩ ካፌ ፕሮጀክትና ሌሎች ጋር በመተባበር ስልጠናው ተግባራዊ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
በዘንድሮ አመትም ለመስክ የሥልጠና ትምህርት ከ800 በላይ አስተባባሪዎች ተገቢውን ስልጠና ወስደው ወደ ተግባር የገቡ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በስልጠና ትምህርት ቤት 30 አርሶ አደሮችን በአንድ ማዕከል በማደራጀት የማሰልጠንና የማስተማር ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
በትምህርት ቤቱ የተደረጁ አርሶ አደሮች በቡና ምርጥ ዘር ብዜት፣ በችግኝ ዝግጅት፣ በግብዓት አቅርቦትና አጠቃቀም፣ የመሰረተ ልማት ተደራሽነት ለማስፋት የሚያስችሉ ተግባር ተኮር ስልጠናዎች እየተሰጡ መሆኑን ገልጸዋል።
የኤክስቴሽኑን አገልግሎትና የራሳቸውን እውቀት በመጠቀም ምርታማና የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ያደርጋቸዋል ነው ያሉት።
ለአርሶ አደሮች እየተሰጠ ያለው የመስክ ስልጠና የቡና ጥራትና ምርታማነትን ለማሻሻል የላቀ ፋይዳ ያለው በመሆኑ የምርምር ተቋማት፣ ዩኒቨርሲቲዎችና ሌሎችም እንዲያግዙ ጠይቀዋል።