አባይ ቴሌቪዥን የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ተሰጠው - ኢዜአ አማርኛ
አባይ ቴሌቪዥን የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ተሰጠው
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 29/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ለአባይ ቴሌቪዥን የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሰጠ።
የቴሌቪዥን ጣብያው እሁድ ታህሳስ 28 ቀን 2016 ዓ.ም “ዋሻው እንዴ” በተሰኘው ፕሮግራሙ ላይ የሴቶችን ስብዕና፣መብትና ክብር የሚያጎድፍ እንዲሁም የህብረተሰቡን መልካም ባህልና እሴት የሚጥሱ በተለይም በሴት ልጆች ላይ የሚፈጸም ወንጀልን የሚያበረታቱ ታዳጊዎችን ላልተገባ ድርጊት የሚዳርጉ ሃሳብና አስተያዬቶችን በፕሮግራሙ ላይ ማስተላልፉን ባለስልጣኑ ባደረገው የሚዲያ ይዘት ክትትልና ግኝት የሚያመላክት ሲሆን ህብረተሰቡም ጥቆማዎች መቅረባቸውን ገልጿል።
አባይ ቴሌቪዥን በተደጋጋሚ የህብረተሰቡን መልካም ዕሴት፣ሰላምና ደህንነት የሚያናጉ ፕሮግራሞችና ዘገባዎችን በጣብያው ሲያሰራጭ ከባለስልጣኑ በኩል በተለያዩ መንገዶች ግብረመልሶችን በመስጠት እንዲሁም ከጣብያው ሃላፊዎች ጋር ውይይትን በማካሄድ መሻሻሎችን እንዲያደርጉ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን አስገንዝቧል።
ጣብያው ግን እነዚህን መሰል ድርጊቶች ለማረም ባለመቻሉ በእለቱ የተሰራጨው ፕሮግራም የመገናኛ ብዙኃን አዋጅን 1238/2013 አንቀጽ 68/2 ለ/ሐ/መ እና ሠ ላይ የተቀመጡ ድንጋጌዎችን የጣሰ ሆኖ መገኘቱን ገልጿል።
በመሆኑም ጣብያው በቀጣይ መሰል ህግን የሚጥሱ ሃላፊነት የጎደላቸው የሰውን ልጅ ስብዕና እና ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ፕሮግራሞችን ከማሰራጨት እንዲቆጠብ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን ባለስልጣኑ አስታውቋል።