ቀጥታ፡

ታዳጊዎችና ወጣቶች በባህል ስፖርቶች ላይ ያላቸውን ተሳትፎ እንዲያጎለብቱ ማድረግ ይገባል - የዘርፉ ባለሙያዎች

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 27/2016(ኢዜአ)፦ታዳጊዎችና ወጣቶች በባህል ስፖርቶች ላይ ያላቸውን ተሳትፎ እንዲያጎለብቱ ማድረግ ይገባል ሲሉ የዘርፉ ባለሙያዎች ተናገሩ።

የብዙ ክፍለ ዘመናት ታሪክ ያለውን የኢትዮጵያ የባህል ስፖርት ትውፊቱን ጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፍ የማድረግ ስራ ይበልጥ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ኢዜአ ያነጋገራቸው የዘርፉ ባለሙያዎች ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አዘጋጅነት "የባህል ስፖርት ለአብሮነትና ለሀገር ግንባታ" በሚል መሪ ሀሳብ 14ኛው ከተማ አቀፍ የባህል ስፖርቶች ውድድርና ፌስቲቫል ትናንት በጉቶ ሜዳ መጀመሩ ይታወቃል።

በዚህ ውድድር በገና እና በሌሎች የባህል ስፖርቶች ላይ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡

በኢትዮጵያ ገበጣን፣ የገና ጨዋታን፣ ፈረስ ጉግስንና የቀስት ኢላማን ጨምሮ 294 የባህል የስፖርት አይነቶች እንዳሉ ተፈራ መኮንን የተባሉ የባህል ስፖርት ተመራማሪ ያካሄዱት ጥናት ያሳያል።

ከእነዚህ የባህል ስፖርቶች መካከል 13ቱ ሕግና ደንብ ወጥቶላቸው በሀገር አቀፍና በክልሎች ደረጃ ውድድር እየተካሄደባቸው የሚገኙ ናቸው።

ገበጣ፣ ገና፣ ፈረስ ጉግስ፣ የቀስት ውድድር፣ ኩርቦ፣ ቡብና ሻህ ህግና ደንብ ወጥቶላቸው ከሚካሄዱ ስፖርቶች መካከል ይጠቀሳሉ።

የአዲስ አበባ የባህል ስፖርት ፌዴሬሽን የበላይ ጠባቂ አቶ ብርሃኑ አድማሱ እንደገለጹት የገና ባህላዊ ጨዋታ ከ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ በኢትዮጵያ ይዘወተር ነበር።

በመዲናዋ የገና ጨዋታን ጨምሮ ሌሎች ባህላዊ ስፖርቶችን ለማሳደግና ከትውልድ ትውልድ ለማስተላለፍ በትምህርት ቤቶች፣ በሆቴሎችና በሌሎች ተቋማትና ስፍራዎች ለማስፋት እየተሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

የጉለሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት የስፖርት ትምህርትና ስልጠና ባለሙያ አቶ ታምራት ሸዋ በቀጣይ ሕዝባዊነቱን ማስፋትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተደራሽ በማድርግ ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ የባህል ስፖርት አሰልጣኞች ማህበር ጸሃፊና አሰልጣኝ አቶ ያረጋል አሰፋ ባህላዊ ስፖርቶች የሕዝቦችን አንድነትና አብሮነት የሚያጠናክሩና ሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍሎች የሚያቅፉ ናቸው ብለዋል።

ወጣቱ በውጭ ሀገራት ስፖርቶች ብቻ ከሚሳብ ባህላዊ ጨዋታዎችን በማስተዋወቅና እሴቶችን ጠብቆ በማቆየት በኩል መገናኛ ብዙሃን የግንዛቤ ስራ ላይ በትኩረት መስራት እንዳለባቸው አመልክተዋል።

በ14ኛው ከተማ አቀፍ የባህል ስፖርቶች ውድድርና ፌስቲቫል በገና ባህላዊ ጨዋታ የሚወዳደሩት አርቲስት ጸጋዬ ዘርፈና አርቲስ ጌትነት ፈይሳ(ጋሽ ጃንቦ) የኢትዮጵያ መልካም እሴቶች እንዲጎለብቱ ለማድረግ የገናን ባህላዊ ጨዋታ ጨምሮ ሌሎች ባህላዊ ስፖርቶችን ለማሳደግ በትብብር መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

በተለይም ወጣቶችና ታዳጊዎች ስለባህል ጨዋታዎች በአግባቡ እንዲያውቁና በውድድሮች እንዲሳተፉ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል።

14ኛው ከተማ አቀፍ የባህል ስፖርቶች ውድድርና ፌስቲቫል እስከ ጥር 9 ቀን 2016 ዓ.ም ይቆያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም