የመግባቢያ ስምምነቱ በሰጥቶ መቀበልና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ ነው

477

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 27/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ እና በሶማሌላንድ መካከል የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት በሰጥቶ መቀበልና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ ነው ሲሉ በሳህል ቀጠና የቀድሞ የአሜሪካ ልዩ መልክተኛና የአትላንቲክ ካውንስል የፖለቲካ ጉዳዮች ተመራማሪ አምባሳደር ጄ ፒተር ፋም ገለጹ።

አምባሳደር ጄ ፒተር ፋም በኢትዮጵያና በሶማሌላንድ መካከል የተደረገውን የመግባቢያ ስምምነት አስመልክቶ ከቢቢሲ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

አምባሳደሩ ስምምነቱ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ ካላት የህዝብ ብዛትና የመልማት አቅም እንዲሁም ከወደብ ኪራይ ዋጋ ውድነት አንጻር በጅቡቲ ወደቦች ላይ ብቻ ጥገኛ ሆና መቀጠል እንደማትችል ከተገነዘበች ቆይታለች ብለዋል።

የመግባቢያ ስምምነቱ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ያለውን ነባራዊ ሁኔታዎች ያገናዘበ፣ በሰጥቶ መቀበልና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ መሆኑንም አብራርተዋል።

በተጨማሪም ስምምንቱ የቀጣናውን አካባቢ ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ ሊያሻሽል የሚችል መሆኑንም አስረድተዋል።

በአውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር በ1960ዎቹ በርካታ ሀገራት ሶማሌላንድን በነጻና ሉአላዊት ሀገርነት እውቅና ሰጥተዋት የነበረ መሆኑን አስታውሰው ግልጽ ባልሆነ ምክንያት ከሶማሊያ ግዛት ጋር እንድትቀላቀል ተደርጓል ነው ያሉት።

ከዚያድ ባሬ አስተዳደር መፈራረስ በኋላ ሶማሌላንድ የራሷ የሆነ ዲሞክራሲያዊ ምርጫዎች በማድረግ የራሷን አስተዳደር መስርታ ከሰላሳ አመታት በላይ መቆየቷንም አስታውሰዋል።

ከኢትዮጵያ ባሻገር ሌሎች ሀገራትም በሶማሌላንድ መዋእለ ንዋያቸውን እያፈሰሱ መሆናቸውን በማውሳት የእንግሊዝ ኩባንያዎች ከተባበሩት አረብ ኤሚሬትሱ ዱባይ ፖርትስ ኩባንያ ጋር በመሆን ቢሊዮን ዶላሮችን በማውጣት በበርበራ ወደብ ልማት ላይ እየተሳተፉ መሆኑን አንስተዋል።

ቢዘገይም ቢፈጥንም፤ ቢፈለግም ባይፈለግም ሶማሊላንድ አለም አቀፍ እውቅና የማግኘቷ ጉዳይ አይቀሬ ነው ሲሉ ተናግረዋል አምባሳደሩ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም