በትግራይ ክልል የተፈጠረው ሰላም የተጎራባች ክልሎች ሕዝቦች ግንኙነትንና የንግድ ልውውጡን እያጠናከረው ነው - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ ክልል የተፈጠረው ሰላም የተጎራባች ክልሎች ሕዝቦች ግንኙነትንና የንግድ ልውውጡን እያጠናከረው ነው
መቀሌ ፤ታኅሣሥ 27/2016 (ኢዜአ)፡- በትግራይ ክልል የተፈጠረው ሰላም የተጎራባች ክልሎች ሕዝቦች ግንኙነትንና የንግድ ልውውጡን እያጠናከረው መሆኑን ነዋሪዎች ገለጹ።
ዛሬ በመቀሌ ከተማ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያነጋገራቸው አስተያየት ሰጪዎች እንዳስታወቁት፤ በትግራይ ክልል እና በአጎራባች ክልሎች የተፈጠረው ሰላም በሕዝቦች መካከል ያለውን ግንኙነት እያጠናከረው መጥቷል።
በአማራ ክልል የላይ ጋይንት ወረዳ ነዋሪና በበግ ንግድ ሥራ የተሰማሩ አቶ አምባው ገዛኸኝ፤ የገናን በዓል ምክንያት በማድረግ 20 በጎች መቀሌ ገበያ ላይ ሸጠው እንዳጠናቀቁ ተናግረዋል።
በተለያዩ ምክንያቶች ተቋርጦ የቆየውን የንግድ ልውውጥና ትስስር አሁን በተፈጠረው ሰላም እንደገና ማንሰራራት መቻሉንም አብራርተዋል።
ሌላው ከ50 በላይ ፍየሎችና በጎችን ወደ መቀሌ ገበያ ያቀረቡት ከሰቆጣ ገጠር ዙሪያ ወረዳ የመጡት አቶ አዳነ ወልደኪዳን በበኩላቸው፤ የተፈጠረው ሰላም በሁለቱም ወገኖች የሚገኙ ነጋዴዎችን ተጠቃሚ ማድረጉን ገልጸዋል።
በእንስሳት ንግድ ሥራ ወደ መቀሌ መመላለስ ከጀመሩ 15 ዓመታት እንዳስቆጠሩ የተናገሩት አቶ አዳነ፤ ባለፉት ዓመታት ተቋርጦ የቆየው የንግድ ልውውጥ እያንሰራራ መሆኑን አስረድተዋል።
የአካባቢው ሰላም ሁኔታ እየተሻሻለ በመምጣቱ አሁን የገበያው አቅርቦት ጥሩ በመሆኑ በተሻለ ዋጋ በግ መግዛታቸውን የተናገሩት ደግሞ የመቀሌ ከተማ ነዋሪው አቶ መዝገበ ሃይለ ሥላሴ ናቸው።
በትግራይ ክልል ደቡባዊ ምስራቅ ዞን እንደርታ ወረዳ በማህበር ያመረቱትን ቀይ ሽንኩርት ወደ አማራ ክልል እየላኩ መሆናቸውን የተናገረው ደግሞ ወጣት ፍስሃ ታረቀኝ የተባለ የማህበሩ አባል ነው።
አሁን ያለው የሁለቱ ክልሎች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማጎልበት የንግድ ልውውጡን በማጠናከርና ማህበራዊ ትስስሩን የማጎልበት ፍላጎት እንዳለው ገልጿል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የንግድና ኤክስፖርት ኤጀንሲ ንግድ ውድድርና የሸማቾች መብት ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ካሳሁን ክንደያ በበኩላቸው፤ በተገኘው ሰላም የአጎራባች ክልሎች የንግድ ማህበረሰብ ግንኙነት እየተጠናከረ መምጣቱን አስታውቀዋል።
በተለይ መንገዶች ከመከፈታቸው ጋር ተያይዞ ከትግራይ ክልል ወደ አጎራባች ክልሎች የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት እንደሚላክ እንዲሁም የእርድ እንስሳት፣ ጤፍና በቆሎ ወደ ክልሉ እንደሚገባ ገልጸዋል።