ቀጥታ፡

በሶማሌ ክልል የሚንቀሳቀሱ የዴሞክራሲ ተቋማት ቅንጅታዊ አሰራራቸውን ማጠናከር አለባቸው- ቋሚ ኮሚቴው

ጅግጅጋ ፤ ታህሳስ 27/2016(ኢዜአ)፦ በሶማሌ ክልል የሚንቀሳቀሱ የዴሞክራሲ ተቋማት ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲጠበቁና እንዲከበሩ ቅንጅታዊ አሰራራቸውን እንዲያጠናክሩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት አሳሰቡ። 

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በሶማሌ ክልል የሚገኙ ለምክር ቤቱ ተጠሪ የሆኑ የዲሞክራሲ ተቋማት የሥራ እንቅስቃሴ ያደረጉትን ምልከታ ለሶማሌ ክልል ምክር ቤት ግብረ መልስ አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል። 


 

የቋሚ ኮሚቴው አባላት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሶማሌ ቅርንጫፍ  ጽህፈት ቤትን፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የጅግጅጋ ጽህፈት ቤትን፣ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የጅግጅጋ ቴሌቪዥን ማሰራጫ ጣቢያን፣ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጅግጅጋ ቅርንጫፍንና የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ተወካዮችን አነጋግረዋል። 

ቋሚ ኮሚቴው በፋፈን ዞን ባቢሌ ወረዳ በቆለጂ ተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ ከሚገኙ ተፈናቃዮች ጋር ተወያይቷል። 

በቆለጂ  መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ተፈናቃዮች በትምህርትና በጤና ተቋማት ተገቢው አገልግሎት እንዲቀርብላቸው የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ አስገንዝበዋል።

የቋሚ ኮሚቴው አባልና የቡድኑ መሪ ወይዘሮ አቦኔ አለም እንዳመለከቱት፤ የምልከታው ዋና ዓላማ የተቋማቱን ቅርንጫፎች ያለፉት አምስት ወራት የሥራ አፈጻጸምና ለኅብረተሰቡ የሚሰጡትን አገልግሎት እያጋጠማቸው ያለውን ተግዳሮት ለመለየትና ምክረ ሀሳብ ለማቅረብ ያለመ ነው ። 

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የዜጎች ሰብዓዊ መብት አያያዝን ለማሻሻል፣ ምርመራ ለማድረግና ተጠያቂነትን ለማስፈን በክልሉ ከሚገኙ የፍትህና የፀጥታ መዋቅሮችና ከሌሎች የዴሞክራሲ ተቋማት ጋር ተባብሮ እንዲሰራ አሳስበዋል። 

የሶማሌ ክልል ምክር ቤት የማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ኢድሪስ ሙሴ ምክር ቤቱ የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ ያቀረቡትን ምክረ ሀሳብ  እንደ ግብዓት በመውሰድ የተሻለ የሥራ አፈጻጸም ለማስመዝገብ ይሰራል ብለዋል።


 

በክልሉ ከሚገኙ የዴሞክራሲ ተቋማት ቅርንጫፍ መስሪያ ቤቶች ጋርም ተባብሮ እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

በክልሉ በተለያዩ ምክንያቶች የተፈናቀሉ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ተፈናቃዮች እንደሚገኙ ገልጸው፣ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ከክልሉ አቅም በላይ በመሆኑ ሌሎች አካላትም ትብብር እንዲያደርጉ ሰብሳቢው ጠይቀዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም