የልማት ማህበሩ በመንግስት የሚሰሩ የልማት ስራዎችን ለማገዝ እያደረገ ያለውን ጥረት አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል - አቶ አለማየሁ ባውዲ

ጂንካ፤ ታህሳስ 27/2016 (ኢዜአ):- የአሪ ልማት ማህበር በዞኑ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችን በማገዝ ረገድ እያደረገ ያለውን አበረታች ተሳትፎ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዋና የመንግስት ተጠሪ አቶ አለማየሁ ባውዲ ገለጹ ።

ልማት ማህበሩ ዛሬ በጂንካ ከተማ 2ኛ ዙር ጠቅላላ ጉባኤውን አካሄዷል።

በጉባኤው ላይ የተገኙት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዋና የመንግስት ተጠሪ አቶ አለማየሁ ባውዲ እንዳሉት ልማት ማህበሩ በመንግስት ያልተሸፈኑ የልማት ክፍተቶችን በመሙላት ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።

በዞኑ ለም መሬት፣ ሰፊ የውሃ አቅምና የሰው ሀብት እንዳለ የገለፁት አቶ አለማየሁ ይህን አቀናጅቶ በማልማት የህዝቡን ኑሮ መለወጥ እንደሚገባ ገልጸዋል።

በመሆኑም ማህበሩ እያደረገ ያለው የልማት ተሳትፎ አበረታች መሆኑን ጠቅሰው የአካቢውን ሀብት ወደ ውጤት በመቀየር የነዋሪውን አዳጊ የልማት ፍላጎቶች ለመመለስ የበለጠ መትጋት እንደሚጠበቅበት ነው ያስገነዘቡት።

የልማት ማህበሩ ከአሪ ህዝብ አልፎ ሌሎች አጎራባች ዞኖችና ወረዳዎችን መጥቀም የሚችልበትን አቅም እንዲያጎለብት ማህበሩን ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባም ተናግረዋል።


 

የማህበሩን ውስን ሀብቶች በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባና ተጨማሪ ሀብት በመፍጠር ረገድ የማህበሩ አባላት ሰፊ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለባቸውም አቶ አለማየሁ አሳስበዋል።

የአሪ ልማት ማህበር ሰብሳቢ አቶ ታፈሰ ተስፋዬ እንደገለፁት፤ ማህበሩ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ዘርፎች በሚያደርገው የልማት ተሳትፎ መንግስትን በማገዝ ነዋሪውን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ለአብነትም ልማት ማህበሩ በጂንካ ከተማ 12 ሼዶችን በመገንባት በስራ ዕድል ፈጠራ የተደራጁ ወጣቶችን የመስሪያና መሸጫ ቦታ እጥረት ለመቅረፍ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በዞኑ የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን መሰረተ ልማት በሟሟላት ረገድ ሰፊ ተሳትፎ ማድረጉን ጠቁመዋል።

ልማት ማህበሩ የአሪ ህዝብ መግባባቢያ ቋንቋ የሆነው ''የአሪ አፍ'' ፊደል ተቀርፆለት በአፍ መፍቻ ቋንቋነት በትምህርት ስርአት ውስጥ እንዲካተት ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን አንስተዋል።

በተጨማሪም ህብረተሰቡን በማስተባበር የገጠር መንገዶችን የመጠገን ስራ ሲሰራ መቆየቱን አንስተው ለአርሶ አደሮችም የምርጥ ዘርና የአፈር ማዳበሪያ ድጋፍ ማድረጉን ጠቁመዋል።

የአሪ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም አታ ማህበሩ በዞኑ ውስጥ የሚሰሩ የልማት ስራዎችን ከመደገፍ አኳያ ባለፉት አመታት ሰፊ ተሳትፎ ሲያደርግ መቆየቱን ገልፀዋል።

የማህበሩ መቋቋም ለዞኑ ትልቅ አቅም እንደፈጠረና በቀጣይም የማህበሩ አባላት ቁጥርን በማሳደግ የልማት አቅሙን ለማጎልበት በተቀናጀ መንገድ ይሰራል ነው ያሉት ።

በጉባኤው ላይ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልልና የአሪ ዞን ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ ባለድርሻ አካላትና የማህበሩ አባላት የተሳተፉ ሲሆን የቦርድ አመራር አባላት ምርጫም ተከናውኗል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም