ቀጥታ፡

በፍርድ ቤቶች የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች በዘመናዊ አሰራር ለማቃለል የሚደረጉ ጥረቶች ሊጠናከሩ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 27/2016(ኢዜአ)፦ በፍርድ ቤቶች የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለማቃለል ዘመናዊ የአሰራር ሥርዓቶችን ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተቀላጠፈ የዳኝነት አገልግሎት መስጠት የሚያስችለውን 'ስማርት ኮርት ሲስተም' የተሰኘ በዘመናዊ የቴክኖሎጂ የታገዘ ሥርዓት ወደ ሥራ አስገብቷል።


 

እነሱም በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በኩል የበለጸጉ ስማርት ቻትቦት፣ አውቶማቲክ ስፒች ትራንስክሪፕሽን፣ ስማርት ኮርት ሩም እንዲሁም መረጃ ዴስክ የተሰኙ አራት መተግበሪያዎች ናቸው።

በማብሰሪያ መርኃ ግብሩ ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ቴዎድሮስ ምህረትና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና የዴሞክራሲ ተቋማት ተወካዮች ተገኝተዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ፣ ተመርቆ ወደ ሥራ የገባው በቴክኖሎጂ የታገዘው አሰራር የዳኝነት አገልግሎትን በማዘመንና ተደራሽ በማድረግ ትልቅ አስተዋጽዖ ያደርጋል።

በዛሬው ዕለት የተመረቁት መተግበሪያዎችም ተገልጋዮች ሳይንገላቱ አገልግሎት እንዲያገኙ፣ ቅሬታን ማቅረብ እንዲችሉና ተጠያቂነት እንዲኖር ለማስቻል ትልቅ ሚና እንዳላቸው ገልፀዋል።

በፍርድ ቤቶች የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ከመሰረቱ ለመፍታት እንደሚያስችሉና የዜጎችን በግልጽ ችሎት የመዳኘት መብት የሚያረጋግጡ መሆኑን ተናግረዋል።

አዲሱ ቴክኖሎጂ ቀልጣፋ፣ ተደራሽ፣ ግልፅ፣ ጥራት ያለው፣ ተገማች እና ተዓማኒነት ያለው የዳኝነት አገልግሎት ለመስጠትም መሰል ቴክኖሎጂዎች ይበልጥ ተደራሽ መሆን እንዳለባቸው ነው ያነሱት።

በቀጣይ ክልሎችን ጨምሮ በሁሉም ደረጃ በሚገኙ ፍርድ ቤቶች ተግባራዊ እንዲሆኑ በቅንጅት መሥራት እንደሚገባ አሳስበው፣ መንግሥት አስፈላጊውን ዕገዛ ያደርጋል ነው ያሉት።

ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይህንን ዘመናዊ አሰራር ወደ ሥራ ማስገባቱ የ2025 የአገሪቱ የዲጂታል ስትራቴጂ እቅድ እንዲሳካ የበኩሉን አስተዋጽዖ ማድረጉንም ተናግረዋል።


 

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ቴዎድሮስ ምህረት በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ቀልጣፋ የተደራጀና ዘመናዊ የዳኝነት አገልግሎት ለማጠናከር ትኩረት ተደርጓል።

በዛሬዕ ዕለት ተመርቆ ወደ ሥራ የገባው አዲሱ በቴክኖሎጂ የታገዘው አሰራርም የዚሁ ጥረት አንዱ አካል መሆኑን ጠቅሰው ዘመናዊ አሰራሩ የዳኝነት አገልግሎቱን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

ዘመናዊ የአሰራር ሥርዓቶች የሥራ ጫና እንዲሁም ወጪ የሚቀንሱ በመሆናቸው በቀጣይም በቴክኖሎጂ የታገዙ አሰራሮች የማስፋት ሥራ ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

የኢንፎርሜሸን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰሎሞን ሶካ እንዳሉት፣ የተቋማትን አገልግሎት ወረቀት አልባና ደህንነት የተጠበቀ እንዲሆን ለኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ልማት ትኩረት ተደርጓል።


 

በጠቅላይ ፍርድ ቤት የተጀመረው ቴክኖሎጂም በአይነቱ ለየት ያለ አዲስ ሲስተም መሆኑን ገልፀው፣ የፍርድ ቤቶችን አሰራር ወደ ተሻለ ደረጃ የማሳድግ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ፣ ግልፅና ተጠያቂነት ያለው አገልግሎት እንዲሰጡ እንደሚያግዛቸው ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና በበኩላቸው፣ የስማርት ኮርት ሲስተም 'ሰው ሰራሽ አስተውሎት በሁሉም' የሚለውን ዕቅድ በተግባር የሚያሳይ መሆኑን ገልፀዋል።

መተግበሪያዎቹ ከደኅነትና ግልጸኝነት ጉዳዮች አኳያ ከፍተኛውን ጥንቃቄ እና የሥነምግባር ጉዳዮችን ታሳቢ በማድረግ የበለፀገ መሆኑን ገልፀዋል።

ከጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች መካከል ዳኛ ሕትመት አሰፋና ዳኛ አበበ ሰለሞን ወደ ሥራ የገቡት ቴክኖሎጂዎች ለዜጎች የተፋጠነ ፍትህ ለመስጠት እንደሚያስችል ተናግረዋል።

በተለይም በችሎት ክርክር ሂደት የሁሉንም ወገኖች ድምጽ ወደ ጽሁፍ መቀየር ማስቻሉ የሰራተኞችን ድካም መቀነስ ብቻ ሳይሆን ትክክለኛ መረጃ ላይ በመመስረት ውሳኔ በመስጠት ለዳኝነት አገልግሎቱ ትልቅ እፎይታ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም