ማዕድ ማጋራት መደጋገፍን፣ አንድነትንና መተሳሰብን የሚያጎላ መልካም እሴት ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
ማዕድ ማጋራት መደጋገፍን፣ አንድነትንና መተሳሰብን የሚያጎላ መልካም እሴት ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 27/2016(ኢዜአ)፦ ማዕድ ማጋራት መደጋገፍን፣ አንድነትንና መተሳሰብን የሚያጎላ መልካም እሴት ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለኃብቶችንና በጎ ፈቃደኞችን በማስተባበር የገናን በዓል ምክንያት በማድረግ በ750 ሚሊየን ብር ወጪ ለ263 ሺህ ወገኖች ማዕድ አጋርቷል።
የማዕድ ማጋራት ሥነ-ሥርዓቱን አስመልክቶ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ባስተላለፉት መልዕክት ማዕድ ማጋራት መደጋገፍን፣ አንድነትንና መተሳሰብን የሚያጎላ መልካም ባህል ነው ብለዋል።
ከተማ አስተዳደሩም ይህን መልካም እሴት በማስቀጠል ረገድ በትኩረት እየሰራ ይገኛል ሲሉም ገልጸዋል።
በተለይም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ዜጎች በዘላቂነት ራሳቸውን የሚችሉበት አማራጮችን ማስፋት ዋነኛ ጉዳይ ስለመሆኑ አንስተዋል።
ሀገራቸውን በእውቀታቸውና በጉልበታቸው ያገለገሉ አረጋውያን፣ እናቶች፣ አካል ጉዳተኞችና ልዩ ድጋፍ የሚሹ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ማገዝና መደገፍ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በመሆኑም ከተማ አስተዳደሩ የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ ለ263 ሺህ ወገኖች 750 ሚሊየን ብር ወጪ የተደረገበት ማዕድ ማጋራቱን ገልጸው ድጋፉ የተደረገው በከተማዋ የሚገኙ ባለኃብቶችንና በጎ ፈቃደኞችን በማስተባበር መሆኑንም ጠቁመዋል።
የማዕድ ማጋራት መርኃ ግብሩ በሁሉም ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ኅብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፍቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር አብርሃም ታደሰ በበኩላቸው በከተማዋ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት እየዳበረና ባህል እየሆነ መጥቷል ብለዋል።
በተለይም በከተማዋ የሚገኙ ባለኃብቶች ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመሆን በተለያዩ የድጋፍ መርኃ ግብሮች ላይ እየተሳተፉ መሆናቸው የሚበረታታና ቀጣይነት ሊኖረው የሚገባ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።
ከተማ አስተዳደሩ የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ ቀደም ሲል ለአቅመ ደካሞች ገንብቶ ያስረከባቸው 389 ቤቶች ከባለሃብቶች ጋር በመተባበር የተገነቡ መሆናቸውን አንስተዋል።
በዛሬው ዕለትም እንዲሁ የተደረገው የማእድ ማጋራት መርኃ ግብር ላይ የከተማዋ ባለኃብቶች የጎላ ሚና ማበርከታቸውን ጠቁመው ስጦታው የፍቅር ማሳያ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ድጋፍ የተደረገላቸው ዜጎች ድጋፉ ''በዓሉን በደመቀ ሁኔታ ለማክበር በእጅጉ ያግዘናል'' ብለዋል።
በመሆኑም የተደረገው ድጋፍ ወጪያቸውን ለማቃለል የሚያግዝ በመሆኑ መደሰታቸውን ጠቁመው ለዚህም ከተማ አስተዳደሩን አመስግነዋል።