አገርን ከልጆቿ ያስተሳሰረ ጥሪ - ኢዜአ አማርኛ
አገርን ከልጆቿ ያስተሳሰረ ጥሪ
ዳያስፖራ ‘dia speiro’ ከሚለው የግሪክ ቃል የመጣ ሲሆን “በተለያየ አገር ወይም የምድር ክፍል ተበትኖ መኖር” የሚለውን ትርጉም ይሰጣል።
በግሪክ አቴና (በአሁኑ አጠራር አቴንስ) የነበረው ቱሲዳይደስ የተሰኘ ግሪካዊ የታሪክ ሰውና ጄኔራል ከክርስቶስ ልደት በፊት በአምስተኛው ክፍለ ዘመን ለመጀመሪያ ጊዜ ቃሉን እንደተጠቀመበት ይነገራል።
በዘመናዊው የሰው ልጅ ታሪክም የተለያዩ ጸሐፍቶች ዳያስፖራ ለሚለው ቃል የተለያዩ ትርጉሞችን የሰጡ ሲሆን ከተወለደበት መልክዐ ምድራዊ አካባቢ ውጭ በተለያዩ አገራት የሚኖር ሕዝብ ነው የሚለው ትርጓሜ ብዙዎችን የሚያስማማ ነው።
በጦርነት፣ በኢኮኖሚያዊ ጥቅም፣ በትምህርትና በሌሎች ምክንያቶች ዜጎች ከአገራቸው ሊሰደዱ ወይም ሊወጡ ይችላሉ።
ከዚህ እሳቤ በመነሳት እ.አ.አ በ2020 በወጣ መረጃ 281 ሚሊዮን ዳያስፖራዎች በተለያዩ ዓለም ክፍሎች እንደሚገኙና ይህም በአማካይ 3 ነጥብ 6 በመቶ የሚሆነው የዓለም ሕዝብ ከአገሩ ውጭ እንደሚኖር የሚያመላክት ነው።
ከአገራቸው ውጭ የሚኖሩ ዳያስፖራዎች ቁጥር እ.አ.አ በ2000 ከነበረበት 173 ሚሊዮን በ2020 ከ281 ሚሊዮን በላይ መድረሱ የዳያስፖራ ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ መሄዱን ያሳያል።
እ.አ.አ በ2019 በወጣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሪፖርት በዓለም ግዙፍ የዳያስፖራ ቁጥር ያላት ሕንድ ስትሆን 17 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሕዝብ ወይም 20 በመቶው የዓለም ዳያስፖራ ድርሻ ትይዛለች።
ሜክሲኮ 11 ነጥብ 8 ሚሊዮን እንዲሁም ቻይና 10 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዳያስፖራዎች በተለያዩ አገራት እንዳሏቸው መረጃዎች ያመለክታሉ።
አፍሪካ 34 ሚሊዮን ዳያስፖራ እንዳላት የሚገለጽ ሲሆን የአፍሪካ ሕብረት እ.አ.አ በ2012 የአፍሪካ ዳያስፖራ የአህጉሪቷ ስድስተኛው ትልቁ ቀጣና ሲል ሰይሞታል።
እ.አ.አ በ2050 የአፍሪካ ዳያስፖራ ቁጥር በሶስት እጥፍ ተመንድጎ 100 ሚሊዮን ይደርሳል የሚሉ ትንበያዎችም በተለያዩ አካላት እየወጡ ይገኛሉ።
ናይጄሪያ፣ ጋና፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ኬንያና ካሜሮን በርካታ ዳያስፖራ ካላቸው የአፍሪካ አገራት መካከል በዋነኝነት ይጠቀሳሉ።
በዓለም የሚኖረው ዳያስፖራ ለዓለም አጠቃላይ ምርት መጠን (ጂዲፒ) 9 ነጥብ 4 በመቶ ድርሻ እንዳለው ይገመታል።
ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ ይፋዊ ጥናቶች ባይኖሩም ከሶስት ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በተለያዩ የዓለም ክፍሎች እንደሚኖሩ ይገለጻል።
በሰሜን አሜሪካና አውሮፓ በርካታ ቁጥር ያላቸው የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች የሚኖሩ ሲሆን በእስያ፣ ኦሺንያ፣ አፍሪካና ደቡብ አሜሪካ አህጉራትም የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች ይኖራሉ።
ዳያስፖራዎቹ ለኢትዮጵያ በሕጋዊ መንገድ ለቤተሰቦቻቸው ገንዘብ በመላክ፣ ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት፣ ለንግድ መሳለጥ፣ ለስራ ፈጠራና በእውቀትና ክህሎት ሽግግር የራሳቸውን አበርክቶ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
ዳያስፖራዎች በተቀናጀ መልኩ ለአገራቸው የሚያደርጉትን ድጋፍ ተቋማዊ በሆነ መልኩ ለመምራት ከአራት ዓመት በፊት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት (በቀድሞ አጠራሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ) መቋቋሙ ይታወሳል።
ተቋሙ ወደ ስራ ከገባበት ጊዜ አንስቶ ዳያስፖራው በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና በተለያዩ መስኮች ያለውን ተሳትፎ ለማሳደግ እየሰራ ይገኛል።
ዳያስፖራው ባለፉት አምስት ዓመታት በአማካይ በየዓመቱ በሕጋዊ መንገድ 4 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ ወደ አገሩ እንደሚልክ የተቋሙ መረጃ ያሳያል።
ለአንድ ሚሊዮን ዳያስፖራና የኢትዮጵያ ወዳጆች ወደ አገር ቤት ጥሪ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በ2014 ዓ.ም ለአንድ ሚሊዮን ዳያስፖራና የኢትዮጵያ ወዳጆች ወደ አገር ቤት ባደረጉት ጥሪ በርካታ ኢትዮጵያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል።
የአንድ ሚሊዮን ዳያስፖራ ወደ አገር ቤት ጉዞ ጥሪ ዓላማ የቱሪዝም ዘርፉን ማነቃቃት፣ በውጭ መገናኛ ብዙኃን ስለ ኢትዮጵያ የሚሰራጨውን ሐሰተኛ መረጃ በመቀልበስ እውነቱን ለዓለም ማሳወቅ እንዲሁም የቱሪስት መዳረሻዎችና የልማት ቦታዎችን ማስተዋወቅ እንደሆነም መገለጹ ይታወቃል።
ጥሪው ከተቀመጠው ግብ አኳያ በተለይ በውጭ መገናኛ ብዙኃን ስለ ኢትዮጵያ የሚሰራጨውን ሐሰተኛ መረጃ በመቀልበስና ቱሪዝምን በማነቃቃት የተሳካ ነበር።
በተጨማሪም ዳያስፖራው ልዩ ልዩ ድጋፎችን በማድረግ ውጤታማ ተግባራትን አከናውኗል።
በአንድ ሚሊዮን የዳያስፖራ ወደ አገር ቤት ጥሪ ጉዞ ከ264 ሚሊዮን ብር በላይ ሀብት ከዳያስፖራው መሰብሰቡን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት መረጃ ያሳያል።
የዳያስፖራው አባላት 114 ሚሊዮን 189 ሺህ 780 ብር የሚያወጣ ድጋፍ ለተፈናቀሉ ወገኖች ማድረጋቸውም ተገልጿል።
ዳያስፖራው 98 ሚሊዮን 805 ሺህ 768 ብር የሚገመት መድሐኒትና የህክምና ግብአቶች ወደ አገር ቤት ይዞ በመምጣት ድጋፍ ማድረጉም እንዲሁ።
የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሮችን በማዘጋጀት 49 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ከዳያስፖራው ማሰባሰብም ተችሏል።
ዳያስፖራው ለበጎ አድራጎት ስራዎች 1 ሚሊዮን 930 ሺህ 560 ብር ድጋፍ ማድረጉንም አገልግሎቱ በወቅቱ አሳውቋል።
በአንድ ሚሊዮን የዳያስፖራ ወደ አገር ቤት ጥሪ በአገርና ክልል አቀፍ ደረጃ 55 ኩነቶች (ኤቨንትስ) መዘጋጀታቸው ተጠቅሷል።
ከኢድ እስከ ኢድ ወደ አገር ቤት ጥሪ
ሌላው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለዳያስፖራው ያቀረቡት ጥሪ ከ"ኢድ እስከ ኢድ የአገር ቤት ጥሪ" ነው።
ዳያስፖራዎችና የኢትዮጵያ ወዳጆች ወደ አገር ቤት በመምጣት በተለያዩ ኩነቶች ላይ ከመሳተፍ ባለፈ ለአገራቸው የኢኮኖሚና ሌሎች ድጋፎችን አድርገዋል።
ከኢድ እስከ ኢድ ወደ ሃገር ቤት ጉዞ ጥሪ መሰረት ወደ አገር ለገቡ ኢትዮጵያውያን የ'እንኳን ደህና መጣችሁ' መርሃ ግብር በወዳጅነት አደባባይ ተካሄዷል።
ጥሪው የኢትዮጵያን ገፅታ ከመገንባትና የቱሪዝም ዘርፉን ከማነቃቃት ባሻገር ለዲፕሎማሲ ስራውም የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል።
በቀረበው ጥሪ መሰረት ወደ አገር ቤት የመጡ አካላት ኢድን በጋራ በማክበር የተቸገሩ ወገኖችን በመጠየቅና በማገዝ ጥሩ ቆይታ ማድረጋቸውን በወቅቱ ተናግረዋል።
በጦርነት ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች ተዘዋውረው በመጎብኘት አቅማቸው የቻለውን ሁሉ ድጋፍ በማድረግም ተሳትፈዋል።
በአገራቸውም ኢንቨስት የማድረግ እድል እንዲፈጠርም ምቹ መደላድል ሆኗል።
ለሁለተኛው ትውልድ ዳያስፖራ ጥሪ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ታህሳስ 13 ቀን 2016 ዓ.ም ለየት ያለ አስተሳሳሪ የሆነና በሶስት ዙር የሚተገበር ለሁለተኛው ትውልድ ዳያስፖራ አባላት የተዘጋጀ ጥሪ አቀረቡ።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ መሰረት የዳያስፖራ አባላቱ ከታህሳስ 20 ቀን 2016 እስከ መስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም በሶስት ዙር ወደ ሀገራቸው እንዲመጡ እየተሰራ ይገኛል።
የመጀመሪያ ዙር ከታህሳስ 20 እስከ ጥር 20/2016 ድረስ የሚቆይ ሲሆን 'Connect to your culture' በሚል መሪ ሃሳብ ይከናወናል። ይህም ባህላቸውን እንዲያውቁና እንዲያስታውሱ ዓላማ ያደረገ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ በመልዕክታቸው ጠቅሰዋል።
ሁለተኛው ዙር ደግሞ 'Connect to your history' በሚል መሪ ሀሳብ በየካቲት ወር 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከሚካሄደው የአፍሪካ ሕብረት ጉባኤ ጀምሮ እስከ ክረምት መግቢያ የሚካሄድ ሲሆን በባህል፣ በቋንቋ እና በሃይማኖት ያሉ ታሪኮችን እንዲያውቁ የሚያስችል ነው ብለዋል።
ሶስተኛው ዙር 'Leave your legacy' በሚል ከ2016 ዓ.ም የክረምት መግቢያ ጀምሮ እስከ መስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም የሚካሄድ ሲሆን ህጻናትን በማስተማር፣ ችግኝ በመትከልና ሌሎች የክረምት በጎ ተግባራት መሳተፍ በሀገራቸው አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ማድረግን ግብ አድርጓል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በውጭ አገራት ለሚኖሩ ሁለተኛ ትውልድ ዳያስፖራ አባላት ጥሪ የተደረገበት ምክንያት፥ ሀገራቸውን እንዲያውቁ፣ እንዲወዱና በቀጣይ ጊዜ ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ኢትዮጵያን እንዲያገለግሉ መሆኑን ገልጸዋል።
ሁለተኛው ትውልድ ዳያስፖራ በሌላ አገር የተወለደና በዚያው የሚኖር ግለሰብ ወይም ዜጋ ማለት ነው።
ሁለተኛው ትውልድ ዳያስፖራ ከትውልድ አገሩ ጋር ያለው ቁርኝት በጣም ያነሰ መሆኑ የሚገለጽ ሲሆን ይህም የሚመነጨው ዳያስፖራው የተወለደበትን አገር የማያውቅና ለሚኖርበት አገር አኗኗርና ታሪክ ይበልጥ የቀረበ ከመሆኑ አኳያ እንደሆነ ይገለጻል።
የዚህ አይነት የዳያስፖራ አባላት ስለ አገር፣ ማንነት ጥርት ያለ አረዳድ እንደሌላቸውና የማንነት ችግር ውስጥ እንደሚገቡ የብራይተን ዩኒቨርሲቲ ጥናት ያመለክታል።
ሁለተኛ ትውልድ ዳያስፖራ ለረጅም ዓመታት በተለያዩ አገራት የኖሩ ዳያስፖራዎችን አስተዋጽኦ የሚተካና ለትውልድ አገሩ በቀጣይ ጊዜያት ትልቅ አበርክቶ ይኖረዋል ተብሎ የሚጠበቅ ነው።
በሌላ አገር የተወለዱ ሁለተኛ ትውልድ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አባላት በተወሰነ መልኩም ቢሆን በበጎ ፈቃድ ስራዎች፣ የኢትዮጵያ መልካም ገጽታ በመገንባትና በእውቀትና ክህሎት ሽግግር ላይ ይሰራሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረቡት ጥሪ በውጭ ሀገራት የተወለዱ ሁለተኛ ትውልድ የዳያስፖራ አባላት ባህላቸውን ይበልጥ እንዲያውቁ ለማስቻልና ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ትስስር የማጠናከር ዓላማ ያለው ነው።
የአድዋ የድል በዓልና ታሪካዊ ክዋኔዎችን ለሁለተኛው ትውልድ ገለጻ የሚደረግበት ሁነትን ጨምሮ የጉዞ መርሐ ግብሮች መዘጋጀታቸው ዳያስፖራው ስለ አገሩ ታሪክ እንዲያውቅና ለማንነቱ እንዲቀርብ ከማድረግ አኳያ አስተዋጽኦ አለው።
ጥሪው በተለያዩ አገራት ለረጅም ጊዜ የኖሩ ዳያስፖራዎች ለአገራቸው ከሚያበረክቱት አስተዋጽኦ በተጨማሪ ሁለተኛው ትውልድ የዳያስፖራ አባላት ለኢትዮጵያ እድገትና ልማት ለሚያደርገው ድጋፍ በር የሚከፍት እንደሆነ ይታመናል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል መሐመድ አል አሩሲ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ ኢትዮጵያ በዓለም አድናቆት ካገኘችባቸው ባህሎቿ፣ ትውፊቶቿና የቱሪዝም መዳረሻዎቿ ባሻገር ሰፊ የልማትና የኢንቨስትመንት እድሎች ያሏት አገር መሆኗን ተናግረዋል።
ከዚህ አኳያ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁለተኛው ትውልድ ዳያስፖራ ጥሪ የኢትዮጵያ ብዝኃ ባህሎችና እሴቶች እንዲሁም ያሏትን እምቅ ሀብቶች ለማወቅ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር አመልክተዋል።
ለዚህም ሁለተኛው ትውልድ ዳያስፖራ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ እንደ መልካም እድል በመጠቀም ወደ እናት አገራቸው በመምጣት ያሉ እድሎችን በመቃኘት ለኢትዮጵያ እድገት እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል።
ትውልደ ኢትዮጵያዊ የምግብ ዝግጅት ባለሙያው ማርከስ ሳሙኤልሰን በበኩላቸው ኢትዮጵያ እምቅ የቱሪዝም ኃብት ያላትና ልትጎበኝ የሚገባት ሀገር እንደሆነች መገንዘብ መቻላቸውን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በውጭ ሀገራት የተወለዱ ሁለተኛው ትውልድ የዳያስፖራ አባላት ወደ ሀገራቸው እንዲመጡ ባቀረቡት ጥሪ መሰረትም በቀጣይ ቤተሰቦቻቸውን ይዘው እንደሚመለስ ተናግሯል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለሁለተኛው ትውልድ ዳያስፖራ አባላት ያደረጉትን ጥሪ ተከትሎ ወደ አገር ቤት ለሚገቡ የዳያስፖራ አባላት የአውሮፕላን ትኬትና የሆቴል መስተንግዶ ዋጋ ቅናሽ ማድረጉን ገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሁለተኛው ትውልድ የዳያስፖራ አባላት ያደረጉትን ጥሪ ተከትሎ ወደ አገር ቤት ለሚገቡት የዳያስፖራ አባላት አየር መንገዱ ከ15 እስከ 20 በመቶ የአውሮፕላን ቲኬት ቅናሽ ማድረጉን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የንግድ ሥራ ዘርፍ ዋና ኃላፊ ለማ ያዴቻ ለኢዜአ ገልጸዋል።
እንዲሁም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ አካል በሆነው የስካይ ላይት ሆቴል ለሚያርፉ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችም በተመሳሳይ ከ15 እስከ 20 በመቶ ቅናሽና ለእንግዶቹም ልዩ ዝግጀት ማድረጉን ዋና ኃላፊው አብራርተዋል።
በተለያዩ አገራት የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና ሚሲዮኖችም ጥሪውን ተከትሎ የተለያዩ ዝግጅቶችን እያደረጉ ይገኛሉ።
በጣሊያን እና ጀርመን የሚኖሩ ወገኖች በሁለተኛው ትውልድ ጥሪ ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ከፍተኛ ፍላጎትና ዝግጁነት ማሳየታቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው በየአገራቱ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለሁለተኛው ትውልድ ዳያስፖራ ያቀረቡትን ጥሪ ተከትሎ የተቋቋመው ዐቢይ ኮሚቴ የዝግጅት ስራዎችን ማጠናቀቁ የሚታወስ ነው።
በዚህም መሰረት ጥሪውን ተከትሎ የመጡ የዳያስፖራ አባላትን የመቀበል ተግባር ተጀምሯል።
ወደ አገር ቤት የመጡ የሁለተኛው ትውልድ የዳያስፖራ አባላትም ሀገራዊ ጥሪውን በመቀበል መምጣታቸውን በመግለጽ ኢትዮጵያን ለማሳደግ እና ለመደገፍ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
ሀገራቸውን መመልከት መቻላቸው የተለየ ስሜት እንደፈጠረባቸው፣ በሀገሪቱ እየተደረገ ያለውን የልማት ስራ በአካል ቀርቦ ለማየት የሚያስችል መሆኑን፣ የሀገራቸውን ባህልና ታሪክ ለማወቅ ጉጉት እንዳደረባቸው ተናግረዋል።
በቆይታቸውም የኢትዮጵያን የልማት ስራዎች በአካል በመጎብኘት ከአገራቸው ጋር ያላቸውን ቁርኝት እንደሚያጠናክሩም ገልጸዋል።
ጥሪው በተለይ ሁለተኛው ትውልድ ዳያስፖራ አገሩን በማወቅና ከማንነቱ ጋር በመተሳሰር በአገሩ ጉዳይ ላይ እንዲሳተፍ የማድረግ አላማን ያነገበ መሆኑን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ገልጿል።
የአገልግሎቱ የዳያስፖራ ማህበረሰብ ልማት ተጠባባቂ ዳይሬክተር አቶ ነብዩ ሰለሞን የሁለተኛው ትውልድ ዳያስፖራ አባላት በጥሪው መሰረት ወደ አገር ቤት በመምጣት ኢትዮጵያን እንዲያውቁና ለአገራቸው ልማትና እድገት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ለአንድ ሚሊዮን ዳያስፖራና የኢትዮጵያ ወዳጆች ወደ አገር ቤት ጥሪ ጀምሮ እስከ ሁለተኛው ትውልድ ዳያስፖራ ድረስ የቀረቡ ጥሪዎች ዳያስፖራው ከአገሩ ጋር ያለውን ትስስር የሚያጠብቁና በአገሩ ጉዳይ ያለውን ተሳትፎ የሚያሳድጉ ናቸው።
እስካሁን ለተደረጉ ጥሪዎች በዳያስፖራው የተሰጡ ተግባራዊ ምላሾችም የሚደነቁ ናቸው፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጥሪ ዳያስፖራውን ከእናት አገሩ ጋር የበለጠ የማስተሳሰርና የማቀራረብ ግብ የሰነቀ በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።