ቀጥታ፡

ሕዝበ ክርስትያኑ በዓሉን ሲያከብር ለሰው ልጆች ፍቅር በመስጠትና በችግር ላይ ያሉ ወገኖችን በማሰብ ሊሆን ይገባል - የሃይማኖት አባቶች

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 27/2016(ኢዜአ)፦ ሕዝበ ክርስትያኑ የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን ሲያከብር ለሰው ልጆች ፍቅር በመስጠትና በችግር ላይ ያሉ ወገኖችን በማሰብ ሊሆን እንደሚገባ የሃይማኖት አባቶች ገለጹ።

የሃይማኖት አባቶቹ በዓሉን በማስመልከት ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ሁሉም ሕብረተሰብ በአንድነትና በጋራ በመቆም መስራት እንዳለበትም አሳስበዋል።

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ባስተላለፉት መልዕክት ቅዱስ ያሬድ የኢየሱስ ክርስቶስን መወለድ ሲገልጽ ''የሰላም ሰንደቅ ዓላማ የሆነ ልጅ ተወለደ'' እንዳለ ሁሉ ልደቱ ለኦርቶዶክሳያውያን የሰላም ምልክት መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም በዓሉ አብሮነት፣ አንድነትና ሰላም የሚበሰርበት መሆኑን ጠቅሰው ሕብረተሰቡ ለሰላም መስፈን የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

በተለይም የሃይማኖት መሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ምሁራን በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚስተዋሉ የሰላም እጦት ችግሮችን ለመፍታት አቅማቸውንና እውቀታቸውን መጠቀም እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።


 

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቀጳጳሳት ብጹዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ ሱራፌል በበኩላቸው የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል እግዚአብሔር ምን ያህል የሰው ልጆችንና ፍጥረታቱን እንደወደደ ማሳያ ነው ብለዋል።

አምላክ ከሰው ልጆች ጋር ያለውን ግንኙነት ለማደስ ሰማይንና ምድርን ለማስታረቅ መወለዱን አንስተው የክርስቶስን መወለድ በአግባቡ ለማክበር ለሰው ልጆች ሕይወትና ለእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን ክብርን መስጠት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።


 

የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ጠቅላይ ፀሃፊ ቄስ ደረጀ ጀንበሩ ምዕመኑ የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን ሲያከብር ለሰው ልጆች ሁሉ ፍቅርን፣ ርህራሄን በማሳየት፣ የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ሁሉም በአንድነትና በጋራ በመቆም መስራት እንዳለበትም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም