ወደብ ከደረሰው ማዳበሪያ ከ83 በመቶ በላይ የሚሆነው ወደ ሀገር ውስጥ ተጓጉዟል - ኢዜአ አማርኛ
ወደብ ከደረሰው ማዳበሪያ ከ83 በመቶ በላይ የሚሆነው ወደ ሀገር ውስጥ ተጓጉዟል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 27/2016(ኢዜአ)፦ ለ2016/17 የምርት ዘመን እስከአሁን በ10 ዙሮች ጂቡቲ ወደብ ከደረሰው የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ ከ83 በመቶ በላይ የሚሆነው ወደ ሀገር ውስጥ መጓጓዙ ተገለጸ።
ወደብ ከደረሰው 4 ሚሊዮን 899 ሺህ 403 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ እስከ ታህሳስ 27 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ 4 ሚሊዮን 73 ሺህ 839 ኩንታል ወደ ሀገር ውስጥ ተጓጉዞ በመሠረታዊ የኅብረት ሥራ ማኅበራት አማካኝነት አርሶ አደሮች ጋር እንዲደርስ እየተደረገ መሆኑም ተመልክቷል።
ትላንት ምሽት 520 ሺህ ኩንታል ዩሪያ የጫነች መርከብ ጂቡቲ ወደብ የደረሰች ሲሆን፣ በመጪዎቹ ቀናት ከፍተኛ መጠን ያለው ተጨማሪ ማዳበሪያ ከውጭ እንደሚጓጓዝ የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን መረጃ ያመለክታል።
የግብርና ሚኒስቴር በየዓመቱ እያጠና በሚያቀርበው የሀገሪቱ የአፈር ማዳበሪያ ፍላጎት መሰረት የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከተቋቋመበት ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ዓለም አቀፍ ጨረታ እያወጣ የማዳበሪያ ግዥ በመፈጸም ላይ ይገኛል።