የመግባቢያ ስምምነቱ በጋራ መልማትን መሰረት ያደረገና ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታን የሚያስገኝ ነው - ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
የመግባቢያ ስምምነቱ በጋራ መልማትን መሰረት ያደረገና ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታን የሚያስገኝ ነው - ምሁራን
ሀዋሳ/መደወላቡ/ሐረር፤ ታህሳስ 27/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ስምምነት በጋራ መልማትን መሰረት ያደረገና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን በሀዋሳ፣ መደወላቡና በሀሮማያ ዩኒቨርሲቲዎች የሚሰሩ ምሁራን ገለጹ።
በኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ በግልፅ እንደተቀመጠው ለጎረቤት ሀገራት ቅድሚያ በመስጠት ችግሮቻቸውን በመጋራት የአካባቢውን ፀጋ በጋራ ለማልማትና ተባብሮ ለማደግ ያለንን ራዕይ ያሳያል ሲል የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሰሞኑን በኢትዮጵያና በሶማሌላንድ መካከል የተፈረመውን የመግባቢያ ስምምነት ተንተርሶ ያወጣው መግለጫ ያስረዳል።
ኢዜአ በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገራቸው በዩኒቨርሲቲዎቹ የሚሰሩ ምሁራንም ስምምነቱ በጋራ መልማትን መሰረት ያደረገና ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን የሚያመጣ መሆኑን አንስተዋል።
የመግባቢያ ስምምነቱ በሀገሪቱ እየተመዘገበ ያለውን ኢኮኖሚያዊ እድገት የሚያፋጥንና የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የሚያግዝ መሆኑንም ገልጸዋል።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲን፣ የትምህርት ክፍሉ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ወገኔ ማርቆስ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ የወደብ ፍላጎት አገሪቱ አሁን እያስመዘገበች ካለችው ኢኮኖሚያዊ እድገት አንጻር ከፍተኛ ድርሻ ያለው ነው።
መንግስት በቅርቡ ይፋ ያደረገውን የወደብ ያስፈልገናል ጥያቄ መሰረት በማድረግ የተጀመረው ስራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ እየታየበት ነው ብለዋል።
ለዚህም በቅርቡ ከሶማሌላንድ ጋር የተደረገው የባህር በር የማግኘትና የመጠቀም የመግባቢያ ሰነድ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
የመግባቢያ ሰነዱ በጋራ መልማትን መሰረት ያደረገ የዲፕሎማሲ ውጤትና በቀጣይ እንዲኖረን ለምንገፈልገው የወደብ ተጠቃሚነት መሰረት የጣለ መሆኑን ተናግረዋል።
ጅማሮው ሌሎች ወደብ ያላቸው ሀገራት ፍላጎት እንዲያሳድሩ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
ስምምነቱን ተከትሎ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶችን ለማቃለል የሰጥቶ መቀበል መርህን የተከተለ የዲፕሎማሲ ስራ ማጠናከር ይገባልም ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ወደብ አልባ በመሆኗ በተለይ በኢኮኖሚ እይታ ብዙ ችግሮች ስታስተናግድ መቆየቷን የጠቀሱት በመደወላቡ ዩኒቨርስቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ባልደረባና የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት አማካሪ አቶ ደጀኔ ጣፋ ናቸው።
ስምምነቱ ወደብ አልባ ሆና የቆየችው ኢትዮጵያ ወደ ውጪ የምትልከውም ሆነ ወደ ሀገር ውስጥ በምታስገባው ምርት ላይ ለዋጋ መዋዠቅና ላልተገባ ግሽበት እንዳትዳረግ ያስችላል ብለዋል።
በቅርቡ ከሶማሌላንድ ጋር የተፈረመው ስምምንት ኢትዮጵያን የወደብ ባለቤት ሊያደርጋት የሚችልና የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ፈተና ወደ እድል የሚቀይር መሆኑንም ገልጸዋል።
ይህም ሀገሪቱን በአለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንድትሆን እንደሚያስችላትም ነው ጨምረው የተናገሩት።
ኢትዮጵያ የወደብ ባለቤትነትና ተጠቃሚነት ጥያቄን አጀንዳ ባደረገች አጭር ጊዜ ውስጥ እመርታዊ ለውጥ እየታየ ነው ያሉት ደግሞ የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል የምጣኔ ሃብት መምህር ፍሬዘር ጥላሁን ናቸው።
ላለፉት 30 ዓመታት ተዳፍኖ የነበረ የወደብ ጉዳይ ሀገሪቱ እያስመዘገበች ካለው ኢኮኖሚያዊ እድገትና አሁን የአለም ገበያ ስርዓት ከሚፈልገው አንጻር በጣም አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
ከሶማሌላንድ ጋር የተደረገው የመግባቢያ ስምምነትም አብዛኞቹ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ከ80 ከመቶ በላይ የንግድ እንቅስቃሴያቸውን በባህር ላይ በሚያደርጉበት ዘመን የተፈጸመ ነው ብለዋል።
ወደብ ያለው ሀገር ኢኮኖሚያዊ ተጽእኖው ከፍተኛ ነው ያሉት መምህሩ ስምምነቱ አስፈላጊ፣ ወቅታዊና አንገብጋቢ መሆኑንም ገልጸዋል።
ስምምነቱ በሀገሪቱ እየተመዘገበ ያለውን ኢኮኖሚያዊ እድገት የሚያፋጥንና የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብም እንደሚያግዝ ምሁራኑ ጠቁመዋል።