ከመቅደላ የተዘረፉት ታሪካዊ ቅርሶች ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ - ኢዜአ አማርኛ
ከመቅደላ የተዘረፉት ታሪካዊ ቅርሶች ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 27/2016(ኢዜአ)፦ የልዑል አለማየሁ ቴዎድሮስ ፀጉር እና በመቅደላ ጦርነት ወቅት በእንግሊዝ ጦር የተዘረፉ ታሪካዊ ቅርሶች ተመለሱ።
የተመለሱት ታሪካዊ ቅርሶች ሁለት በብር የተለበጡ ዋንጫዎች፣ አንድ የቀንድ ዋንጫ፣ ደብዳቤዎች እንዲሁም አንድ ጋሻ ከእንግሊዝ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል።
በእንግሊዝ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር የሆኑት ተፈሪ መለሰ ቅርሶቹን ይዘው የመጡ ሲሆን ለቅርሶቹ የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ተቀብለዋል።
ቅርሶቹን ማስመለስ መቻሉ ለኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ድል መሆኑንም አምባሳደር ተፈሪ ተናግረዋል።
በእንግሊዝ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቅርስ አስመላሽ ኮሚቴና ሼኸራዛድ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር ባለፈው መስከረም ወር ላይ ቅርሶቹን ማስመለሳቸው ይታወሳል።
መንግስት ተዘርፈው በተለያዩ ሀገራት ሙዚየም የሚገኙ ቅርሶችን ለማስመለስ የሚያደርገውን ዲፕሎማሲያዊ ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል መባሉን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።