ቀጥታ፡

ኅብረተሰቡ በዲጂታል አማራጮች የበዓል ግብይትን መፈፀም እንዲችል በቂ ዝግጅት አድርገናል - ባንኮች

አዲስ አበባ ፤ታህሳስ 26/2016 (ኢዜአ)፦  ኅብረተሰቡ ያለምንም ውጣውረድ በዲጂታል አማራጮች የበዓል ግብይትን በመፈፀም የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲያገኝ ለማስቻል በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን ባንኮች ገለፁ።  

በበዓላት ወቅት አስፈላጊ የሆኑ የፍጆታ እቃዎችን መሸመት የሁልጊዜ የተለመደ ተግባር ነው።  

ታዲያ እነዚህን ተግባራት ለመከወን ጥሬ ብርን ይዞ መንቀሳቀስ ራስን ለሥርቆት የሚያጋልጥ ከመሆኑ ባሻገር በገበያው ውስጥ የኃሰተኛ የብር ኖት ሥርጭት እንዲስፋፋም እድል እየሰጠ ነው።

በመሆኑም ኅብረተሰቡ ሳይጉላላ ግብይቱን በእጅ ስልኩ እንዲፈፅምና ገንዘብ በቀላሉ ለመላክ የዲጂታል አማራጮች የተሻሉ ሆነው መቅረባቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው የባንክ ኃላፊዎች ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጂታል ባንኪንግ ዲቪዥን የመርቸንትና የኤጀንት ማኔጅመንት ዳይሬክተር አቶ ብሌን ኃይለሚካኤል እንዳሉት ዲጂታል ባንኪንግ ኅብረተሰቡ ክፍያዎችን በቀላሉ በኤቲ ኤም ካርዶችና በእጅ ስልኩ የሚፈፅምበት መንገድ ነው። 

ዲጂታል ባንኪንግ የሰዎችን ድካምና ወጪ የሚቀንስና እንደ አገርም መደበኛ ባልሆነ መንገድ የሚቀመጥን ገንዘብ ወደ ሥርዓቱ በማስገባት ባንኮች በቂ የሆነ ገንዘብ አግኝተው ብድር ማቅረብ እንዲችሉ የሚጠቅም ነው ብለዋል።

ባንኩ በተለይም በመጪው የገና በዓል በሲቢኢ ብር፣ በሞባይልና ኢንተርኔት ባንኪንግ እንዲሁም በኤቲ ኤምና ፖስ ማሽን አማራጮች ለደንበኞቹ የዲጂታል ባንኪንግ አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀቱን  ገልጸዋል።


 

የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ የዲጂታል ፋይናንሺያል ሰርቪስ ሲኒየር ዳይሬክተር አቶ አብዲ ፈቀደ በበኩላቸው ዘመኑ የዲጂታል መሆኑን ተከትሎ የደንበኞች ፍላጎትና የባንኮች አሰራር አብሮ እየተቀየረ እንደሆነ አንስተዋል። 

የዲጂታል አሰራር ሥራን የሚያቀል እንደሆነ አንስተው የበዓል ሰሞን ሰዎች ከባንኮች ጋር ያላቸውን ግንኙነት የሚጨምርበት ወቅት እንደሆነም ተናግረዋል።

ባንኩ ደንበኞቹ በዲጂታል መንገድ ተጠቅመው ግብይት እንዲፈፅሙና ብድርንም ማግኘት የሚችሉበትን አሰራር መዘርጋቱን አስረድተዋል።

በበዓል ሰሞን በዲጂታል መንገድ የሚደረጉ ግብይቶች እንዲሁም የብድር ፍላጎት እንደሚጨምርም ነው ኃላፊዎቹ የተናገሩት።

ባንኮቹ ደንበኞቹ በበዓል ወቅት ለሚፈፅሟቸው ግብይቶች በቂ ገንዘብን በኤቲ ኤም ማሽኖቻቸው በኩል ለማቅረብ መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል።

ደንበኞች የበዓል ግብይታቸውን በዲጂታል ባንኪንግ በመፈፀም ያለምንም ውጣውረድ አገልግሎት ማግኘት እንደሚችሉም ተናግረዋል። 

ኅብረተሰቡ በበዓሉ ወቅት "ሽልማት ደርሶኸል የምደውልልህ ከባንክ ነው" በማለት ከሚያጭበረብሩ ግለሰቦች እንዲጠነቀቅ ጥሪ ቀርቧል።  

 

         

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም