ቀጥታ፡

ኅብረት ሥራ ማኅበራት ለአርሶና አርብቶ አደሩ ምርታማነት ማደግ የሚጫወቱትን ሚና ማጠናከር አለባቸው

አዲስ አበባ ፤ታህሳስ 26/2016(ኢዜአ)፦ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ለአርሶና አርብቶ አደሩ ምርታማነት ማደግ የሚጫወቱትን ሚና ማጠናከር እንደሚገባቸው የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ አመለከቱ። 

አገር አቀፍ የኀብረት ሥራ ማህበራት የለውጥ ንቅናቄ /ሪፎርም/ በአዲስ አበባ ይፋ ተደርጓል።


 

ሪፎርሙ የኅብረት ሥራ ማኅበራት በግብርና፣ በቁጠባና ብድር፣ በኢንቨስትመንት መስክ የሚጫወቱትን ሚና ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ያለመ ነው ተብሏል።  

በሪፎርሙ ይፋ ማድረጊያ ሥነ-ሥርዓት ላይ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ሌሎች የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል። 

የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚረዱ ግብዓቶች በማቅረብ አምራቹ ባመረተው ልክ ተጠቃሚ እንዲሆን በማድረግ ረገድ አበረታች ጅምሮች አሉ።  

እንዲያም ሆኖ ቴክኖሎጂዎችን በጥራትና በብዛት ማቅረብና ገበያን መረጋጋት አሁንም የበለጠ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ነው ያመለከቱት። 

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ሁሉን አቀፍ ለውጥ እንዲያመጡ በመስኩ የለውጥ ሥራዎችን ማጠናከር ወሳኝ ሲሆን ሚኒስቴሩም በዚህ ረገድ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል። 

ሚኒስትሩ እንዳሉት፤የኢትዮጵያ ኀብረት ሥራ ኮሚሽን ማህበራትን ለማጠናከር እንዲሁም የላቀ ሚና እንዲጫወቱ ለማድረግ የሚከናውኑ ተግባራት ውጤታማ እንዲሆኑ ይሰራል ።

የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ጌታቸው መለሰ በበኩላቸው በገንዘብ ቁጠባና ብድር ኅብረት ሥራ ማኅበራት በኩል 50 ቢሊየን ብር በቁጠባና በዕጣ ማሰባሰብ ተችሏል።


 

በዚህም ለአርሶና አርብቶ አደሩ በአማካይ በዓመት 12 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ ብድር እየቀረበ መሆኑን ገልጸው ይህም በመስኩ እየገጠሙ ያለውን የፋይናንስ እጥረት በመፍታት ረገድ ወሳኝ ድርሻ እየተጫወተ ነው ብለዋል።

የኅብረት ሥራ ማኅበራቱ የንግድ እንቅስቃሴዎችን በመደገፍ፣ በድርቅ የተጎዱ ወገኖችና እንዲሁም የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብሮች ላይ በመሳተፍ ወገናዊ ግዴታቸውን እየተወጡ መሆኑንም አብራርተዋል። 

ኅብረት ሥራ ማኅበራት በግብርና ግብዓት፣ ቴክኖሎጂ ቅርቦት፣ በምርት ገበያ እሴት መጨመርና መሰረተ ልማት አቅርቦት ላይ የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑ ርብርብ ይደረጋል ነው ያሉት። 

የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን መረጃ እንደሚያሳየው በአሁኑ ወቅት በገጠርና በከተማ ከ28 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ አባላት ያሏቸው ከ110 ሺህ በላይ መሰረታዊ ኅብረት ሥራ ማኅበራት አሉ።

403 ዩኒየኖች እንዲሁም 5 ፌደሬሽኖች ያሉ ሲሆን በአጠቃላይ ኅብረት ሥራ ማኅበራቱ በግብርና፣ በሸማቾች፣ በቁጠባና ብድርና በሌሎች ዘርፎች ተደራጅተው ከ49 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ማፍራት መቻላቸውን የኮሚሽኑ መረጃ ያመለክታል።      

 

       

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም