ቀጥታ፡

ኃይማኖታዊና ህዝባዊ በዓላትን በሰላም ማክበር የሚያስችል የጸጥታ ዝግጅት ተደርጓል - ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል

አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 26/2016(ኢዜአ)፦ ኃይማኖታዊና ህዝባዊ በዓላትን በተሟላ ሰላምና ደህንነት ማክበር የሚያስችል የጸጥታ ዝግጅት መደረጉን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ።

ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የገና በዓል እንዲሁም ጥምቀት በመላ ሀገሪቱ በድምቀት የሚከበሩ በዓላት ናቸው።

ህብረተሰቡ እነዚህን በዓላት ያለምንም የጸጥታ ስጋት በሰላም ማክበር እንዲችል ፖሊስ ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጓል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጋር በመቀናጀት አዲስ አበባን ሰላምና ደህንነቷ የተጠበቀ፤ ለነዋሪዎቿ ምቹ ከተማ ለማድረግ ሰፋፊ ህግ የማስከበር ዘመቻ /ኦፕሬሽን መስራቱን ገልጸዋል፡፡

በዚህም የነዋሪዎችን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ የሚያስችሉ ውጤታማ ስራዎችን ማከናወን መቻሉን ገልጸው፤ በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። 

በየካቲት ወር በአዲስ አበባ የሚካሄደው የአፍሪካ የመሪዎች እና የሥራ አስፈፃሚዎች ስብሰባ ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲካሄድ አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁንም ተናግረዋል።

በዚህም በአዲስ አበባ በተሰራ የህግ ማስከበር ዘመቻ በተለያዩ የወንጀል ተግባራት በመሳተፍ የተጠረጠሩ ግለሰቦችና ኤግዚቢቶች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የጸጥታ ስጋት ባለባቸው ክልሎች ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር የተቀናጀ የህግ ማስከበር ዘመቻ እያከናወነ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል መላኩ ፈንታ በበኩላቸው በቀጣይ የሚከናወኑ ህዝባዊ በዓላትን ያለምንም የጸጥታ ችግር ለማክበር በቂ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።


 

በዚህም በሁሉም አካባቢዎች የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ማረጋገጥ የሚያስችል የጸጥታ አካላት ሥምሪትና ምደባ መደረጉን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የዜጎችን ሰላምና ደንነት ለመጠበቅ የሚያስችለውን ዝግጅት ማድረጉን ገልጸው፤ ለውጤታማነቱ ደግሞ የህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

"ፖሊስ ያስተባብራል፤ የጸጥታው ባለቤት ግን ህዝቡ ነው" ያሉት ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል መላኩ ፈንታ፤ ህብረተሰቡ አካባቢውን በመጠበቅና መረጃ በመስጠት የተለመደ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አስተላልፈዋል።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም