ቀጥታ፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ የበጎ ፈቃድ መርሃ ግብሮች እንዲሳኩ ድጋፍ ያደረጉ አካላትን አመሰገኑ

አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 26/2016(ኢዜአ)፦ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የከተማ አስተዳደሩን ጥሪ ተቀብለው የበጎ ፈቃድ መርሃ ግብሮች እንዲሳኩ ድጋፍ ያደረጉ አካላትን አመሰገኑ።

ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው የክረምት የበጎ ፈቃድ መርሃ ግብራችንን በማጠናቀቅ የበጋ የበጎ ፈቃድ ጥሪያችንን በመቀበል በርካታ ልበ ቀና ባለሃብቶችና ተቋማት ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛሉ ብለዋል።

ከነዚህም ውስጥ የኢፌዴሪ የገቢዎች ሚኒስቴር እና የጉምሩክ ኮሚሽን ለነዋሪዎች የቤት ግንባታ በትላንትናው ዕለት ያስጀመሩ መሆናቸውን ጠቅሰው በአጭር ጊዜ ውስጥ ግንባታውን በማጠናቀቅ እንደሚያስረክቡን ቃል ስለገቡልን በነዋሪዎቻችን ስም ላመሰግናችሁ እወዳለሁ! ብለዋል።


 

በተጨማሪም ትላንት የተጀመረውን ጨምሮ ለነዋሪዎች የተላለፉትን 389 ቤቶች በመገንባቱ በኩል የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ቲኤንቲ ኮንስትራክሽን ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት፣ ሃቢታት፣ ፍሊንት ስቶን ሆምስ የኢትዮጵያ ጤና ኢንስቲትዩት፣ አቶ ሙኒር ሃይረዲን ፤ዶክተር ዳንኤል እና የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግን አመስግነዋል።

በተጨማሪም ለብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት፣ ለአቶ ቢኒያም ካሳ፣ ለየሰላም ፍሬ ማህበር፣ ለየሳይንስና ኢኖቬሽን ቢሮ፣ ለየአዲስ አበባ ውበትና አረንጏዴ ልማት ቢሮ፣ ለአቶ ፋሲል ዘውዴ እንዲሁም በጋራ ሐብት በማሰባሰብ ቤቶቹን ለገነቡ ግለሰቦች እና ተቋማት በሙሉ ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም