37ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ እና 44ኛው የአስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባዎች በሰላም እንዲጠናቀቁ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት መደረጉ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
37ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ እና 44ኛው የአስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባዎች በሰላም እንዲጠናቀቁ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት መደረጉ ተገለጸ
አዲስ አበባ ታህሳስ 26/2016(ኢዜአ)፦37ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ እና 44ኛው የአስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባዎች በሰላም እንዲጠናቀቁ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አድርጎና ስምሪት ወስዶ ወደ ስራ መግባቱን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይል ገለፀ።
የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይል ለብዙሃን መገናኛ በላከው መግለጫ 37ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ እና 44ኛው የአስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባዎች በሰላም እንዲጠናቀቁ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ወደ ስምሪት መግባቱን አስታውቋል።
ወቅቱ የገና እና የጥምቀት በዓላት የሚከበሩበት እንዲሁም የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ የሚካሄድበት በመሆኑ የሀገራችንን ሰላምና ደኅንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠበቅ በሚያስችል ዕቅድ እየተመራ የፀጥታ ተግባሩን እያከናወነ እንደሚገኝ የጋራ ግብረ-ኃይሉ መግላጫ አስታውቋል።
ከዚህም ጎን ለጎንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለ2ኛ ትውልድ ባቀረቡት የዲያስፖራ ጥሪ መሠረት እንግዶቹ መግባት በመጀመራቸው ሰላምና ፀጥታን በሚገባ ለማረጋገጥ አስተማማኝ የፀጥታ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን የጠቀሰው መግለጫው በሽብርተኞችና በፅንፈኛ ኃይሎች ላይ የማያዳግም ሕጋዊ እርምጃ እየተወሰደ ነው ሲልም አመላክቷል።
የአፍሪካ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ የፀጥታ አካላት ባካሄዱት የተቀናጀ ኦፕሬሽን ስጋት የሚፈጥሩ የወንጀል ድርጊቶችን በከፍተኛ ደረጃ በመቆጣጠር ሰላሟ የተረጋገጠ ከተማ ለመፍጠር የተጠናከረ የፀጥታ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን የጋራ ግብረ-ኃይሉ በመግለጫው አረጋግጧል።
በቀጣይ በሀገራችን የሚካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔን ጨምሮ ሀይማኖታዊና መንግሥታዊ ሁነቶች በሰላም ተጀምረው እንዲጠናቀቁ ኅብረተሰቡ ከፀጥታ አካላት ጎን ሆኖ እያደረገ ያለውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል የጋራ ግብረ-ኃይሉ ጥሪን አቅርቧል።
ኢትዮጵያ በጉባዔው የሚሳተፉ የተለያዩ ሀገራት መሪዎችንና ሌሎች እንግዶችን ለማስተናገድ በተሰጣት ኃላፊነትና በተጣለባት እምነት ልክ ደህንነታቸውን መጠበቅ ከፀጥታ አካላቱ እንደሚጠበቅ የገለፀው የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይሉ መግለጫ ይህንኑ የሚመጥን በተግባር የተደገፈ ልምምድና በቂ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አክሎ ገልጿል፡፡