ቀጥታ፡

የኢትዮጵያና ሶማሌላንድ ስምምነት ቀጣናዊ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ በመፍታት የጋራ ተጠቃሚነትን በሰጥቶ መቀበል መርህ የሚያጸና ነው  

በኢትዮጵያና ሶማሌላንድ መካከል በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ወታደራዊ መስኮች ሰፋ ያሉ የትብብር አድማሶችን ያካተተ ሁሉን አቀፍ የትብብርና አጋርነት የመግባቢያ ሰነድ በቅርቡ መፈረሙ ይታወቃል።

ስምምነቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ፣ በኢትዮጵያ የተፈራረሙ ሲሆን ኢትዮጵያ በኤደን ባህረሰላጤ ላይ የባሕር ኃይል ቤዝና ኮሜርሻል ማሪታይም አገልግሎት በሊዝ የምታገኝበትን ዕድል የሚያስገኝ ነው። 

ሶማሌ ላንድ ደግሞ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሊዙ የሚታሰብ ድርሻ እንዲኖራት የሚያስችል ሲሆን ከዚያም ባሻገር በሂደት ሶማሌ ላንድ ዕውቅና ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግሥት በጥልቀት አጢኖ አቋም የሚወስድበትን አግባብም ያካተተ መሆኑ ተገልጿል።

እዚህ ስምምነት ላይ ከመደረሱ አስቀድሞ ግን በርካታ ውስብስብ ሂደቶች መታለፋቸው እሙን ነው። ለአብነትም የባህር በር ጉዳይን ማንሳት እንደ ነውር እየታየ ሶስት አስርታት አልፈዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዚህ መንገድ መቀጠል አዳጋች መሆኑን በመጥቀስ የባህር በር ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ መሆኑን በግልጽ ቋንቋ አስረድተዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከባህር በር አለመኖር ጋር ተያይዞ ሊመጡ የሚችሉ ውስጣዊ ችግሮችን ለአብነትም ከሕዝብ ቁጥር መጨመር ጋር የሚመጣጠን አገራዊ እድገት የማስመዝገብ ፈተና፣ እንዲሁም የፖለቲካና ደኅንነት ሥጋቶችን ለመቀልበስ ቀደም ሲል አገሪቷ የነበራትን የወደብ አጀንዳ አስፈላጊነት በተመለከተ ኃሳቡ ዳግም እንዲነቃቃ አድርገዋል።

እስካሁን የኢትዮጵያ የዓለም ምጣኔ ኃብታዊ ገበያ ተደራሽነት የሚሳለጠው በጅቡቲ በኩል ሲሆን ለዚህም ኢትዮጵያ ከፍተኛ ክፍያ ትፈጽማለች። ይህም በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአካባቢው በሚከሰቱ ከባድ ሁኔታዎች አማካይነት ከፍተኛ ጫና እያሳደረ ነው። 

በቀይ ባህር ላይ የሚካሄደው ወታደራዊ ቅርምት የኢትዮጵያ ምጣኔ ኃብት መሰረት የሆኑት ማዳበሪያና ነዳጅ ላይ  ተጽዕኖ እያሳዳረ ነው፤ ኢትዮጵያ ያላትን ጥቅም ያለ ባህር ሃይል ማስከበር እንደማይቻል አንድሪው ኮሪብኮ የተባለ ጸሀፊ ቮይስ ኦፍ ኢስት በተሰኘ ድረ ገጽ ላይ በጻፈው ትንታኔ አመላክቷል።

እነዚህ ተደራረቢ ችግሮች በፍጥነት እያደገ ከመጣው የሕዝብ ቁጥር ጋር ተዳምረው ኢትዮጵያ ከባህር በር አለመኖር ጋር ተያይዞ ሊያጋጥሟት የሚችሉት ችግሮች መፍትሄ ካልተገኘላቸው አካባቢያዊ ውጥንቅጥ ሊያሰከትሉ እንደሚችሉም ጠቁሟል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለዚህ ችግር ሁነኛ መፍትሄ ቅድሚያ ሰጥተዋል የሚለው ጸሀፊው ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የደረሰችው የመግባቢያ ሥምምነት ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ እርምጃ መሆኑን ያነሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለንግድና ለባህር ኃይል ቤዝ የሚሆን የሊዝ ወደብ ለማግኘትና በምትኩ ደግሞ ከኢትዮጵያ ኩባንያዎች ድርሻ ለመስጠት ለተለያዩ አገራት ሃሳብ ማቅረባቸውን የሚገልጸው አንድሪው ኮሪብኮ ይሁንና አገራቱ ይህንን ሃሳብ ለመቀበል ፍቃደኝነት አለማሳየታቸውን በትንታኔው አመላክቷል። 

የባህር በር ያላቸው አንዳንድ አገራት ኢትዮጵያ ያቀረበችውን ሃሳብ እንደ ሥጋት የማየት አዝማሚያ

ከማሳየታቸውም በላይ፣ ኢትዮጵያ የጎረቤት አገራትን ልትጠቀልል ነው የሚል የተሳሳተ የመረጃ ጦርነት የከፈቱ አካላት መኖራቸውንና  ይህም አሁንም ድረስ መቀጠሉን ያነሳል።

ይህ ሁኔታ ኢትዮጵያዊያንን ቢያስቆጭም የባህር በር ባለቤት በሆኑት አገራት ዘንድ ግን ምክንያታዊ ምላሽ ተደርጎ ተወስዷል።

ፀሃፊው፣ ኢትዮጵያ በሰላማዊ መንገድ የባህር በር ለማግኘት ያነሳችው አጀንዳና በሂደትም ከሶማሌላንድ ጋር የደረሰችው የመግባቢያ ሥምምነት ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ክንውን መሆኑን ያስረዳል። ይህም ሁነኛ መፍትሄ የኢትዮጵያን የባህር በር ጥያቄ ይፈታል፤ የባህር በር ካለመኖር ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችንም እንደሚያቃልል ይጠቅሳል።

ሶማሌላንድ የአፍሪካ ቅርምትን ተከትሎ በእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ሥር የቆየች ሲሆን እአአ ጁን 26 ቀን 1960 ነጻነቷን አግኝታለች። በወቅቱ በርካታ ሀገራት እውቅና ሰጥተዋት እንደነበርም ይታወሳል። ሆኖም በዚያው ዓመት ከአምስት ቀናት በኋላ በጣሊያን ቅኝ ግዛት ቆይታ ነፃ ከወጣችው ሞቃድሾ ጋር በፈቃዷ ተቀላቅላለች።

በ1991 እ.አ.አ ዳግም ነጻነቷን አውጃ በተከታታይ ሰላማዊ ምርጫ ሰከን ያለ የመንግሥት ቅይይር በማካሄድ ለ30 ዓመታት ዴሞክራሲን በመለማመድ ላይ ትገኛለች። ኢትዮጵያን ጨምሮ አንዳንድ ሀገራት በሐርጌሳ ቆንስላ ጽ/ቤት ከፍተውም ይንቀሳቀሳሉ።

ሶማሌላንድ ምንም እንኳን እስካሁን የተሟላ ዕውቅና ባታገኝም የወደብ አገልግሎትና ልማትን ጨምሮ ከአንዳንድ ሀገራት ጋር ስምምነት ፈርማለች። ከዚህ ቀደም በርበራ ላይ ለኢትዮጵያ የ19 በመቶ ድርሻ እንዲኖራት ይፈቅድ የነበረ የመግባቢያ ሰነድ ተፈርሞ እንደነበርም ይታወሳል።

የኢትዮጵያ መንግስት በቅርቡ ባወጣው መግለጫ በአሁኑ ወቅት ሌሎች ሀገራት ተመሳሳይ ሂደት እየተከተሉ መሆኑን በመግለጽ ኢትዮጵያ የወታደራዊ ቤዝና ኮሜርሻል ማሪታይም አገልግሎት በሰጥቶ መቀበልና በኪራይ ለማግኘት የተፈራረመችው የመግባቢያ ሰነድና ሂደትም በመሠረቱ አንድና ያው መሆኑን ገልጿል።

አንድሪው ኮሪብኮ በትንታኔው በኢትዮጵያና በሶማሌ ላንድ መካከል የተደረሰውን ስምምነት በተሣሣተ መረጃ በመሣል በአካባቢው ውጥረት እንዲጨምር የተሳሳተ መረጃ በስፋት የሚያሰራጩ አካላት መኖራቸውን ያነሳል። 

ለአብነትም ግብጽ፣ ኢትዮጵያ በሰላማዊ መንገድ የምታደርገውን ጥረት ለማስተጓጎል የተሳሳተ ምክንያት በማቅረብ በታላቁ የህዳሴ ግድብ አማከይነት ከኢትዮጵያ ጋር ሰጣ ገባ ውስጥ የገባች አገር መሆኗን ይጠቅሳል።

እነዚህ የፖለቲካና የደኅንነት ሥጋቶች ተገማቾች ናቸው የሚለው ጸሀፊው ምንም እንኳን ሶማሊያ ለመንግሥታቱ ድርጅት ቅሬታ ብታቀርብም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም ከላይ የተቀመጡትን የሚበጀውን ነገር ከማግኘት አኳያ እነዚህን ስጋቶች መቆጠጣር እንደሚቻል አውቀውታል ሲል ይገልጻል። 

አንድሪው ኮሪብኮ በኢትዮጵያና ሶማሌላንድ የተፈረመው ሁሉን አቀፍ የመግባቢያ ስምምነት በወስጡ ከያዛቸው ጉዳዮች መካከል በሂደት ሶማሌ ላንድ ዕውቅና ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግሥት በጥልቀት አጢኖ አቋም የሚወስድበትን አግባብ መካተቱን በበጎ እንደሚመለከተው ያነሳል።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫና የፓን አፍሪካኒዝምና የጸረ ኢምፔሪያሊዝም ንቀናቄ መነሻ ከመሆኗ አንጻር የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እርምጃ በአፍሪካ ጉዳይ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ይኖረዋል። ይህም በሶማሌላንድ በበርበራ ወደብ መዋዕለ ነዋይ ፈሰስ እያደረገች ያለችውንና ከኢትዮጰያ ጋር መልካም ግንኙነት ያላት የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶችን ጨምሮ ሌሎች አገራት የኢትዮጰያን ፈለግ እንዲከተሉ ያስችላል ባይ ነው።  

ኢትዮጵያ ይህንን የመግባቢያ ሥምምነት በፈረመችበት በተመሳሳይ ቀን ብሪክስን በይፋ ተቀላቅላለች። ይህም ኢትዮጵያና ሶማሌላንድ ያደረጉትን ስምምነት ቻይናና ሩስያ እንዳይቃወሙ በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና ይኖረዋል ይላል።    

ሁለቱ የዶንባስ ሪፐብሊኮች በሩስያ እውቅና ሊያገኙ በታቀረበቡት የመጨረሻው ሰዓት ከነበራቸው ነጻነት ሶማሌላንድ የተሻለ ነጻነት አላት የሚለው ጸሀፊው ያም ብቻ ሳይሆን ሶማሌላንድ ግዛቷን በመቆጣጠር ወይም በማስተደዳር ረገድ ዩክሬን ሁለቱ የዶንባስ ሪፐብሊኮች ላይ ከነበራት የአስተዳደር ሚና በእጅጉ የተሻለ መሆኑን ያነሳል። 

ምንም እንኳን የሶማሊያና የሩስያ ግንኙነት እየተጠናከረ ቢሆንም በሞቋዲሾ ጥያቄ የ125 ዓመታት ግንኙነት ያላትን ኢትዮጰያ በማውገዝ የዜሮ ድምር ፖለሲ ታራምዳለች ተብሎ አይጠበቅም ባይ ነው። ኢትዮጵያን በማውገዝ ሩስያ በዶንባስ ላይ ላይ ያላትን አቋም አታቃልልም ሲልም ይሞግታል።  

ሩስያ የምትከተለውን ገለልተኛ የውጭ ግንኙነት ፖለሲ መሰረት በማድረግ ሶማሊያ ከሶማሌላንድ፣ ከኢትዮጵያና ከተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ጋር ያላትን ልዩነት በሰላማዊ መልኩ እንድትፈታ ጥሪ ታቀርባለች የሚል እምነቱን ይገልጻል። 

ከወታደራዊ፣ ከዲፕሎማሲያዊና የምጣኔ ኃብት አቅም አንጻር የሚታየውን ቀጣናዊ የኃይል ሚዛን ከግምት በማስገባት በሶማሌላንድ ጦርነት ይፈጠራል የሚል ስጋት እንደሌለውና ይህንንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ሥምምነቱ ከመፈረሙ አስቀድሞ እንዳጤኑት ያብራራል። ነገር ግን ሶማሊያ በሥምምነቱ ያላት ቅሬታ እስከቀጠለና ኤርትራና ግብጽ ለራሳቸው ዓላማ እስከተጠቀሙበት ድረስ ውጥረቶች ሊኖሩ  እንደሚችሉ ይጠቁማል።   

በሂደት የኢትዮጵያ ጎረቤት አገራት ኢትዮጵያ ከኩባንያዋ ድርሻ በመስጠት በሊዝ ወታደራዊና የንግድ ወደብ ለማግኘት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረቡትን ሃሳብ ውድቅ ለማድረግ የወሰኑትን ውሣኔ ዳግም ያጤኑታል። 

ይህም ለቀጣናዊ የትሰስር ኮሪደር መጎልበት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ገልጾ በአከባቢው የኢንቨስትመንት ፍሰቱን ለመጨመር እንደሚያስችል ያስረዳል። በዚህም ዓለም ከአንድ ዋልታ ወደ የተለያዩ የምጣኔ ኃብትና ፖለቲካዊ ዋልታዎች ሽግግር ለማድረግ ባለችበት በዚህ ወሳኝ ወቅት ላይ የአፍሪካ ቀንድ ትልቅ ሚና እንዲጫወት ያስችላል ይላል።   

ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏን ተከትሎ ከአገሪቱ ለመጠቀም ፍላጎት እንዳይኖር የሚያደርጉ አካላት ባይታጡም፤ በኢትዮጵያና ሶማሌላንድ የተደረሰው የመግባቢያ ሥምምነት በራሱ ትልቅ የዲፕሎማሲ እርምጃ መሆኑን ማሳነስ ግን አይችሉም። 

የኢትዮጵያና ሶማሌላንድ ስምምነት ቀጣናዊ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመቅረፍ የሚያስችል የጋራ ተጠቃሚነትንም በሰጥቶ መቀበል መርህ የሚያጸና ስምምነት መሆኑን አስረግጠው ያነሳሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም