ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ሥምምነት የጋራ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ሥምምነት የጋራ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ነው
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 26/2016(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ሥምምነት በጋራ ለማደግና በቀጠናው ሠላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንደሚያበረክት ተገለጸ።
ሶማሌላንድ የአፍሪካ ቅርምትን ተከትሎ በእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ሥር የቆየች ሲሆን እንደ አውሮፓውያኑ አቆጠጣር 1960 ነጻነቷን አግኝታለች።
በወቅቱ በርካታ አገራት እውቅና ሰጥተዋት እንደነበርም ይታወሳል። ሆኖም በዚያው ዓመት ከአምስት ቀናት በኋላ በጣሊያን ቅኝ ግዛት ቆይታ ነፃ ከወጣችው ሞቃድሾ ጋር በፈቃዷ ተቀላቅላለች።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጠጣር በ1991 ዳግም ነጻነቷን አውጃ በተከታታይ ሰላማዊ ምርጫ ሰከን ያለ የመንግሥት ቅይይር በማካሄድ ለ30 ዓመታት ዴሞክራሲን በመለማመድ ላይ ትገኛለች።
ኢትዮጵያን ጨምሮ አንዳንድ አገራት በሐርጌሳ ቆንስላ ጽህፈት ቤት ከፍተውም ይንቀሳቀሳሉ።
በመሆኑም ኢትዮጵያም ከሶማሌላንድ ጋር በምጣኔ ኃብት፣ በዲፕሎማሲ፣ በወታደራዊና በሌሎች ዘርፎች ላይ ውል በማሰር በጋራ መሥራት ትችላለች ሲሉ ነው በድሬድዋ ዩኒቨርስቲ የሕግ ትምህርት ቤት ዲን ዶክተር ሮባ ጴጥሮስ የሚናገሩት።
ከዚህ አንጻር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ የተፈረመው ሥምምነት ተገቢነት ያለው መሆኑን ጠቁመዋል።
አንዳንድ አገራት በሶማሌላንድ ወታደራዊ መቀመጫ ወደብ ሲጠይቁ እንደነበር አንስተው አሁን ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ ለመሥራት ሥምምነት ላይ ስትደርስ ደግሞ ተቀባይነት እንደሌለው ለማስመሰል የሚደረገው አካሄድ ትክክል አለመሆኑን አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘት የሚያስችላትን የመግባቢያ ሥምምነት ማድረጓ ትልቅ የዲፕሎማሲ ስኬት መሆኑን ገልጸዋል።
ሥምምነቱ አብሮ ለማደግ፣ በቀጠናው ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት፣ ትብብርን ለማጠናከር ትልቅ ፋይዳ ያለው መሆኑን ገልጸው ይህ እውን እንዲሆን በታሪክ አጋጣሚ የተገኘውን ስኬት ከዳር ለማድረስ መሥራት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ኃላፊነት መሆኑን ተናግረዋል።
በአሶሳ ዩኒቨርስቲ የማኅበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ ዲንና የታሪክ ተመራማሪ ዶክተር አበበ አኖ፤ በኢትዮጵያና በሶማሌላንድ መካከል የተደረገው የመግባቢያ ሥምምነት የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ታሪካዊ ሥምምነት ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከ30 ዓመታት በላይ ወደብ አልባ ሆና የቆየች አገር መሆኗን አስታውሰው ሥምምነቱ የባህር በር ለማግኘት የሚያስችላት መሆኑን ጠቁመዋል።
ሥምምነቱ ከድኅነት ለመውጣት፣ ሰላም ለማስፈንና በምስራቅ አፍሪካ የሚኖራትን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሚና የሚያጠናክር መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ለተደረገው ሥምምነት ተፈጻሚነት በመሥራት በቀጣይም ተጨማሪ የባህር በር ለማግኘት የጀመረውን ጥረት እንዲያጠናክር ጠቁመዋል።