ቀጥታ፡

ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን የሕዳሴ ግድብን እንዲጎበኙና በአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር እንዲሳተፉ ዝግጅት ተደርጓል

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 26/2016(ኢዜአ)፦በጠቅላይ ሚኒስትር  ዐበይ አሕመድ (ዶ/ር) ጥሪ ወደ አገር ቤት የሚመጡ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን በአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር አንዲሳተፉና የታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እንዲጎበኙ ዝግጅት መደረጉ ተገለጸ።

በክረምት ወቅት ወደ ሀገራቸው የሚመጡ ዳያስፖራዎችም በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እንዲሳተፉ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትር  ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ታህሳስ 13/2016 ዓ.ም የዝሆን ዳና ሎጅን  መርቀው በከፈቱበት ወቅት በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው እንዲመጡ ጥሪ አቅርበዋል።

በዚሁ መሰረት ጥሪውን ተቀብለው እየመጡ ላሉ የዳያስፖራ አባላት ከዛሬ ጀምሮ አቀባበል ማድረግ ተጀምሯል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው ሚኒስትሮችም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሶስት ዙር ወደ ሀገር ቤት እንዲመጡ ጥሪ ላቀረቡላቸው ኢትዮጵያውያን ስለ ሀገራቸው እንዲያውቁ የተለያዩ ዝግጅቶች መደረጋቸውን አንስተዋል።

ሁለተኛ ተውልድ ኢትዮጵያውያን እና ወላጆቻቸው በኢትዮጵያ የልማትና የሰላም ጉዞ ላይ ትልቅ  አበርክቶ እንዳላቸው ገልጸው፤ ባሉበት አገር ሁሉ ለአገራቸው ገፅታ ግንባታ እየተጉ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ኃብታሙ ኢተፋ፥ ከቱሪዝም ሚኒስቴርና ሌሎች ተቋማት ጋር በመተባበር ዳያስፖራዎች ልዩ ልዩ መዳረሻዎችን እንዲጎበኙ እንሰራለን ብለዋል።

ኢትዮጵያ በርካታ ሊጎበኙ የሚችሉ የቀድሞ ትውልድና የአሁን ትውልድ አሻራ ያረፈባቸው ፕሮጀክቶች እንዳሏትም አንስተዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሲገነባ በአገር ውስጥ ከሚኖረው ህዝብ በተጨማሪ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በገንዘብ፣ በዲፕሎማሲና በመረጃ ድጋፍ በማድረግ ታሪክ መጻፋቸውን ተናግረዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ ወደ አገር ቤት እየገቡ ያሉ ኢትዮጵያውያንም በግድቡ ግንባታ አበርክቶ እንዳላቸው ጠቅሰው የገነቡትን ግድብ እንዲጎበኙ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን አንስተዋል።


 

የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ በበኩላቸው፥ በሦስተኛ ዙር ወደ አገር ቤት የሚመጡ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን 'leave your legacy' በሚል ከክረምት ወቅት ጀምሮ እስከ መስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ እንዲመጡ ጥሪ መደረጉን ገልጸዋል።

በዚህ ወቅት ኢትዮጵያውያን ችግኝ በመትከልና ሌሎች የበጎ ፈቃድ ሥራዎችን የሚሰሩበት  በመሆኑ ዳያስፖራዎችም በተለያየ መልኩ አሻራቸውን እንዲያኖሩ ይደረጋል ብለዋል።

የግብርና ሚኒስቴርም በመጪው የክረምት ወቅት ወደ አገራቸው የሚመጡ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውረው ችግኝ በመትከል ለሀገራቸው አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም