ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚኖራትን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያስችላታል 

ሐዋሳ ፤ ታህሳስ 26/2016 (ኢዜአ)፦  ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ በዓለምአቀፍ ደረጃ የሚኖራትን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ባለፈ ከሃያላን አገሮች ጋር በትብብር ለመስራት ሰፊ እድልን ሊፈጥርላት እንደሚችል የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተናገሩ።

ምሁራን እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ ያለው ኢኮኖሚያዊ እድገት፣ አምራች የሰው ሃይልና ሌሎች አቅሞች ብሪክስን ለመቀላቀል ተመራጭ አድርጓታል።

የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተከታታይና የርቀት ትምህርት ክፍል ዳይሬክተር ዶክተር ለገሰ ጉዱራ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ብሪክስ እንደ አፍሪካ በማደግ ላይ ላሉ አገሮች ጠቃሚና ፍላጎታቸውን ማሟላት የሚያስችል ማዕቀፍ መሆኑንም አብራርተዋል።

የብሪክስ አባል አገሮች ኢትዮጵያን በተለያየ መንገድ ሲደገፉ የቆዩ መሆናቸውን የጠቀሱት ዶክተር ለገሰ፤ የአገሪቷ የልማት ስራን የሚያግዝ የብድር አገልግሎት ከማግኘት ጀምሮ በትብብር ለመስራት የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል።

በአገሪቷ ያለው ኢኮኖሚያዊ እድገት፣ ከፍተኛ የሰው ሃይል፣ ሰላምና መረጋጋት ኢትዮጵያ ብሪክስን እንድትቀላቀል እድል መፍጠሩንም ገልጸዋል።


 

በዩኒቨርሲቲው የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲን፣ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ወገኔ ማርቆስ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀል ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጠቀሜታ ያለው ነው ብለዋል።

ይህም ለአገሪቷ ትልቅ የዲፕሎማሲ ስኬት መሆኑን ገልጸው፤ የልማት ተግባራትን ለማከናወን የሚያጋጥመውን የገንዘብ እጥረት ለማቃለል የሚያስችል አማራጭ እንደሚያስገኝም አመልክተዋል።

በብሪክስ አባል አገሮች መካከል የሚደረግ የገበያ ትብብር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርና ፖለቲካዊ መደጋገፍም ኢትዮጵያን ተጠቃሚ እንደሚያደርጋት ጠቁመዋል።

አብዛኞቹ የብሪክስ አባል አገሮች በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች ለኢትዮጵያ ድጋፍ የሚያደርጉ መሆናቸውን ያስታወሱት ዶክተር ወገኔ፤ በዚህ ማዕቀፍ መቀላቀል "ዘርፈ ብዙ ተጠቃሚነትን ያረጋግጣል" ብለዋል።

በመሆኑም የተገኘው እድል በአገሪቷ ኢኮኖሚ ላይ ለውጥ እንዲያስመዘግብና የህዝቡን ኑሮ እንዲለውጥ እንዲሁም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ምሁራን አማራጭ ሃሳቦችን በማቅረብ መንግስትን መደገፍ እንደሚጠበቅባቸውም ገልጸዋል።



 

ብሪክስ በቀደሙት ዘመናት በአሜሪካና ሩሲያ ብቻ የተገደበው ሃያልነት ሌሎችም እንዲቀላቀሉ እድልን የፈጠረ መሆኑን የገለፁት ደግሞ በዩንቨርሲቲው የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር ዶክተር ገብረክስቶስ ኑሪዬ ናቸው።

የምዕራባውያን ሃያልነትን ይዞ የመቆየት እሳቤና ተግባር የብሪክስ አገሮችን እንደፈጠረ የጠቀሱት ምሁሩ፤ የብሪክስ አባል አገሮችም አሁን ላይ የዓለምን ኢኮኖሚ እየተቆጣጠሩ ያሉና ተደማጭነት ያላቸው መሆናቸውን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያም ከነዚህ ሃያላን አገሮች ጋር ህብረት መፍጠሯ "ደኅንነትን ለማስከበርና በትብብር ለመስራት ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው" ብለዋል።

እንደ ምሁራኑ አስተያየት እንደአገር የተገኙ እድሎች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዲያስገኙ ለፖሊሲ አውጪዎች ግብዓት የሚሆኑ የምርምር ስራዎችን ማከናወንና ለህዝቡ ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል።

 

 

  

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም