የሁለተኛው ትውልድ ዳያስፖራ ጥሪ ዳያስፖራው ሀገርን በማወቅ በኢትዮጵያ ጉዳይ ተሳትፎ የሚያደርግበትን ሁኔታ የመፍጠር ዓላማ አለው - ኢዜአ አማርኛ
የሁለተኛው ትውልድ ዳያስፖራ ጥሪ ዳያስፖራው ሀገርን በማወቅ በኢትዮጵያ ጉዳይ ተሳትፎ የሚያደርግበትን ሁኔታ የመፍጠር ዓላማ አለው
አዲስ አበባ ፤ታህሳስ 26/2016 (ኢዜአ)፦ የሁለተኛው ትውልድ ዳያስፖራ ጥሪ ዳያስፖራው ሀገሩን በማወቅና ከማንነቱ ጋር በመተሳሰር በሀገሩ ጉዳይ ላይ እንዲሳተፍ የማድረግ አላማን ያነገበ መሆኑን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ገለጸ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ታህሳስ 13 ቀን 2016 ዓ.ም ለሁለተኛው ትውልድ ዳያስፖራ ወደ ሀገር ቤት እንደሚመጡ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።
በዚሁ መሰረት ጥሪውን ተቀብለው እየመጡ ላሉ የዳያስፖራ አባላት ከዛሬ ጀምሮ አቀባበል ማድረግ ተጀምሯል።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት የዳያስፖራ ማኅበረሰብ ልማት ተጠባባቂ ዳይሬክተር አቶ ነብዩ ሰለሞን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በ2014 ዓ.ም "የአንድ ሚሊዮን ዳያስፖራ የሀገር ቤት ጥሪ" እና "ከኢድ እስከ ኢድ ወደ ሀገር ቤት ጥሪ" ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።
በርካታ ኢትዮጵያውንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጥሪውን ተቀብለው ወደ ሀገር ቤት መምጣታቸውን ገልጸው በወቅቱ በርካታ ሁነቶች ተዘጋጅተው ዳያስፖራው የነቃ ተሳትፎ ማድረጉን አመልክተዋል።
አሁን የተደረገውም ጥሪም ከዚህ ቀደም የተደረጉ ጥሪዎች ቀጣይ ምዕራፍ መሆኑን ነው የገለጹት።
ሀገር የሚገነባው በትውልድ ቅብብሎች በመሆኑ ጥሪው ከዚህ አኳያ ቀደምት አባቶች ጠብቀው ያስረከቧትን ኢትዮጵያ በቅርበትን ለመመልክት እድል የሚፈጥር መሆኑን አመልክተዋል።
የሁለተኛው ትውልድ ዳያስፖራ ጥሪ ዓላማ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሀገራቸው ተፈጥሮ ታሪክና ባህል በማወቅ ከሕዝባቸው ጋር ያለውን ትስስር የማጠናከርና በቀጣይ በሀገራቸው ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ እንዲያደርጉ የማድረግ አላማ ያለው ነው ብለዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ መሰረት "Back to your Origin" በሚል መሪ ሀሳብ የዳያስፖራ አባላቱ ከታህሳስ 20 ቀን 2016 እስከ መስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም በሶስት ዙር ወደ ሀገራቸው እንዲመጡ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ስራውን የሚያስተባብር ብሔራዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
የመጀመሪያ ዙር ከታህሳስ 20 እስከ ጥር 20/2016 ድረስ የሚቆይ ሲሆን 'Connect to your culture' በሚል መሪ ሃሳብ ይከናወናል።
በዚህ ሁነት ዳያስፖራዎቹ ባህላቸውን እንዲያውቁና እንዲያስታውሱ የሚያስችላቸው መርሐ ግብሮች እንደተዘጋጁ ነው አቶ ነብዩ ያብራሩት።
ሁለተኛው ዙር ደግሞ 'Connect to your history' በሚል መሪ ሀሳብ በየካቲት ወር 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከሚካሄደው የአፍሪካ ሕብረት ጉባኤ ጀምሮ እስከ ክረምት መግቢያ የሚካሄድ ነው።
ይህ ዝግጅት የዳያስፖራ አባላቱ በባህል፣ በቋንቋ እና በሃይማኖት ያሉ ታሪኮችን እንዲያውቁ ማስቻልን ግቡ አድርጓል።
ሶስተኛው ዙር ደግሞ 'Leave your legacy' በሚል ከ2016 ዓ.ም የክረምት መግቢያ ጀምሮ እስከ መስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም ይከናወናል።
እንደ አቶ ነብዩ ገለጻ፤ በዚህኛው ዙር ሕጻናትን ማስተማር፣ ችግኝ መትከልና ሌሎች ሰፋፊ የበጎ ፈቃድ ተግባራት በማከናወን በሀገራቸው አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ማድረግን ዋንኛ አላማ አድርጓል።
ጥሪውን ተቀብለው ለሚመጡ ዳያስፖራዎች ይፋዊ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት እንደሚካሄድም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ሳምንት የሚል የኢትዮጵያን ባህል የሚያሳይ ዝግጅት፣ የእደ ጥበብ አውደ ርዕይና ባህላዊ ውዝዋዜዎች ለዳያስፖራ አባላቱ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
የቱሪዝም መዳረሻዎችን የሚጎበኙበትን ጨምሮ የተለያዩ የጉዞ መርኃ ግብሮች እንደሚኖሩ ጠቅሰው ሁለተኛው ትውልድ ዳያስፖራ እውቀቱንና ልምዱን ለኢትዮጵውያን የሚያጋሩበት የትስስር መድረኮች እንደሚኖሩም ነው ዳይሬክተሩ ያስረዱት።
የሁለተኛው ዳያስፖራ አባላት በጥሪው መሰረት ወደ ሀገር ቤት በመምጣት ኢትዮጵያን እንዲያውቁና ለሀገራቸው ልማትና እድገት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።