የሕብረት ስራ ማህበራት የልማትና ዕድገት ሪፎርም ይፋ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
የሕብረት ስራ ማህበራት የልማትና ዕድገት ሪፎርም ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 26/2016(ኢዜአ)፦ የሕብረት ስራ ማህበራትን የካፒታል አቅምና አርሶና አርብቶ አደሮች የሚጠቀሙባቸውን ቴክኖሎጂዎች ማሻሻልን ታሳቢ ያደረገ ሀገር አቀፍ የሕብረት ስራ ማህበራት ሪፎርም ይፋ ሆኗል።
የሪፎርሙ ማብሰሪያ መርሃ-ግብር በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡
የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ህብረት ስራ ማህበራት የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ፣ ለግብርና ምርቶች ገበያ በማፈላለግ፣ በገበያ ላይ ዋጋ በማረጋጋትና ቁጠባና ኢንቨስትመንት በማበረታታት ረገድ ቁልፍ ሚና አላቸው፡፡
ህብረት ስራ ማህበራት ከተቋቋሙበት ዓላማ አኳያ የሚጠበቀውን ውጤት ባለማምጣታቸው የተጠናከረ የለውጥ እርምጃ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ዛሬ ይፋ የተደረገው ሪፎርም የህብረት ስራ ማህበራትን የሀገር ውስጥና የውጭ ገበያ ድርሻ ለማሳደግ ሚናው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም የዘርፉን አደረጃጀት ለማጠናከርና አሰራሩን ለማሻሻል ሚኒስቴሩ የሚጠበቅበትን ድርሻ ለመወጣት ቁርጠኛ ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ጌታቸው መለሰ በበኩላቸው በገንዘብ ቁጠባና ህብረት ስራ ማህበራት በኩል 50 ቢሊዮን ብር ቁጠባ ማሰባሰብ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
በዚህም ኮሚሽኑ በአማካይ ከ12 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር በማቅረብ ምርትና ምርታማነት በፋይናንስ ምክንያት እንዳይስተጓጎል ሚናውን እየተወጣ መሆኑን አብራርተዋል፡፡