ቀጥታ፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የገናና ጥምቀት  በዓላት በሠላም እንዲከበሩ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል- የክልሉ ፖሊስ 

አሶሳ ፤ታህሳስ 26/2016(ኢዜአ)፦ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የገናና የጥምቀት በዓላት በሠላም እንዲከበሩ  አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ሃሩን ኡመር ለኢዜአ እንደገለጹት የክልሉ ፖሊስና ሌሎች የጸጥታ ኃይሎችና ተባባሪ አካላት መጪዎቹ በዓላት ያለ ምንም የጸጥታ ችግር እንዲከበሩ ተገቢው ዝግጅት ተደርጓል፡፡

ለዚህም በክልሉ የሚገኙ የፌዴራል ፖሊስና የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ያካተተ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ሥራ መገባቱን አስታውቀዋል፡፡

ግብረ ኃይሉ የጸጥታ ስጋት ሊሆኑ የሚችሉ አካባቢዎችን በጥናት በመለየት በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

የክልሉ ነዋሪዎች የአካባቢያቸውን ሰላምና ጸጥታ ተቀናጅቶ እንዲያስከብር እየተደረገ መሆኑን የተናገሩት ኮሚሽነር ሃሩን፣ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተሰማሩ ወጣቶችም ግብረ ኃይሉን በማገዝ ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

ክልሉ ከአጎራባች አማራና ኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ጋር የጀመራቸው የጸጥታ ማስከበር ሥራዎችም  ማጠናከሩንም ኮሚሽነሩ አብራርተዋል፡፡

ኅብረተሰቡ ከበዓሉ አከባበር ጋር በተያያዘ ሰላምና ጸጥታውን ሊያደፈርሱ የሚችሉ አጠራጣሪ ጉዳዮች ሲያጋጥሙት ለጸጥታ ኃይሎች ጥቆማ እንዲሰጥ አሳስበዋል፡፡

በአሶሳ ከተማ አስተዳደር የወረዳ አንድ ፖሊስ አዛዥ ምክትል ኮማንደር በላቸው ፈረደ በበኩላቸው በወረዳው የጸጥታ ማስከበር ሥራውን የሚያግዙ ቡድኖች ተቋቁመው ወደ ሥራ መግባታቸውን ገልጸዋል፡፡

በወረዳው ወጣቶች በበጎ ፈቃደኝነት ተደራጅተው የአካባቢያቸው ሰላምና ጸጥታ በማስከበር የጸጥታ ኃይሎች ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ በጎ ፈቃደኛ አቶ ታደለ ንጋቱ የተባሉ የወረዳው ነዋሪ ናቸው፡፡

እርሳቸው እንዳሉት ከፖሊስ ጋር ተቀናጅተው በመስራታቸው በአካባቢያቸው በተለይም የዘረፋና ስርቆት ወንጀል ቀንሷል ብለዋል፡፡

''መጪዎቹ በዓላት በሠላም እንዲከበሩ ከጸጥታ ኃይሎች ጎን ሆነን የበጎ ፈቃድ አገልግሎታችንን እንሰጣለን'' ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም