ኢትዮጵያና ሶማሌ ላንድ የተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት ለአህጉራዊ የኢኮኖሚ ልማት በጥሩ ማሳያነት የሚጠቀስ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያና ሶማሌ ላንድ የተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት ለአህጉራዊ የኢኮኖሚ ልማት በጥሩ ማሳያነት የሚጠቀስ ነው

አዲስ አበባ፤ታህሳስ 25/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያና ሶማሊ ላንድ የተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት ለአህጉራዊ የኢኮኖሚ ልማት በጥሩ ማሳያነት የሚጠቀስ መሆኑን አሜሪካዊው የአፍሪካ ፖለቲካ ኢኮኖሚ ጉዳዮች ተንታኝ ላውረንስ ፍሪማን ገለጹ።
ኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘት የሚያስችላትን የመግባቢያ ስምምነት ከሶማሌላንድ ጋር መፈራረሟ ይታወቃል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር ) እና የሶማሌ ላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ ስምምነቱን ተፈራርመዋል።
የመግባቢያ ስምምነቱን በሚመለከት ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት አሜሪካዊው የአፍሪካ ፖለቲካ ኢኮኖሚ ጉዳዮች ተንታኝ ላውረንስ ፍሪማን ስምምነቱ ለአህጉራዊ የኢኮኖሚ ልማትና እድገት በጥሩ ምሳሌነት የሚጠቀስ መሆኑን ገልጸዋል።
ለኢትዮጵያና ሶማሌ ላንድ የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካና ወታደራዊ ትብብርም የላቀ ፋይዳ ያለው መሆኑን ነው ያብራሩት።
ከአፍሪካ ከፍተኛውን ቁጥር ከያዙት አገራት መካከል የምትጠቀሰው ኢትዮጵያ ለረጅም ዓመታት ያለ ባህር በር መቆየቷ ጉዳቱ ከፍተኛ መሆኑን አስታውሰው የአሁኑ ስምምነት የጋራ ተጠቃሚነትና ሰፊ የመልማት እድል እንደሚፈጥርላት ጠቅሰዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያ የባህር በር የምታገኝበትን የመግባቢያ ስምምነት ከሶማሌ ላንድ ጋር መፈራረሟ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ነው የተናገሩት።
በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር የሚያቀጣጥሉ የፖለቲካ ሃይሎች መኖራቸውን የጠቀሱት የፖለቲካ ተመራማሪው እንዲህ አይነት እኩይ ተግባር ለቀጣናው የማይበጅ ነው ሲሉ አብራርተዋል።
በአፍሪካ እምቅ የተፈጥሮ ሃብቶችን በጋራና በትብብር በማልማት መጠቀም ለአህጉራዊ እድገት ወሳኝ በመሆኑ ለግጭትና ጦርነት የሚያነሳሱ ሃይሎችን ማስቆም ይገባልም ነው ያሉት።
የኢትዮጵያና ሱማሌ ላንድ የባህር በር ስምምነት በአህጉራዊና ዓለም አቀፍ የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስሮች ኢትዮጵያን ይበልጥ ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ግዙፍ ምጣኔ ሃብትና በርካታ የህዝብ ቁጥር ያላት አገር በመሆኗ የባህር በሩን በመጠቀም ትልቅ የባህር ሃይል ለመገንባት ያስችላታል ሲሉ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗም ለምጣኔ ሃብት እድገቷ ተጨማሪ እድል መሆኑን ጠቅሰው አዲስ ትብብርን የሚፈጥር ስለመሆኑም አንስተዋል።