የአማራ ክልል ከነበረበት ቀውስ በአጭር ጊዜ ሙሉ በሙሉ ወጥቷል - አቶ ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
የአማራ ክልል ከነበረበት ቀውስ በአጭር ጊዜ ሙሉ በሙሉ ወጥቷል - አቶ ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 25/2016(ኢዜአ)፦ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ጋር በመተባበር ለአማራ ክልል የኮሙኒኬሽን ባለሞያዎች በዲጂታል ሚዲያና በኮሙኒኬሽን የሥራ ሂደት ላይ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ እንዴት ጥቅም ላይ መዋል እንደሚችል በተግባር የተደገፈ ሥልጠና ሰጥተዋል፡፡
በስልጠናው ማጠናቀቂያ መርሐግብር ላይ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ተመስገን ጥሩነህ ባስተላለፉት መልዕክት የአማራ ክልል ከነበረበት ቀውስ በአጭር ጊዜ ሙሉ በሙሉ መውጣቱን ገልፀዋል፡፡
በቀጣይ ለክልሉ መረጋጋት የኮሙኒኬሽን ባለሞያዎች አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ በቴክኖሎጂ የታገዘ ስራ መስራት ውጤታማ እንደሚያደርጋቸውም አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ እድሪስ ስልጠናው የኮሙኒኬሽን ባለሞያዎች ሰላምን፣ ልማትና ሀገራዊ ብልፅግና በሚመጥን ቴክኖሎጂ እየታገዙ ለሕዝብ ተደራሽ እንዲያደርጉ አቅም እንደሚፈጥርላቸው አመላክተዋል፡፡
የአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ መንገሻ ፈንታው(ዶ/ር) በበኩላቸው ሥልጠናው የክልሉን የኮሙኒኬሽን አቅም ለማዳበር ጉልህ ሚና እንደሚኖረው መግለፃቸውን ከአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡