ቀጥታ፡

የጋራ መግባቢያ ስምምነቱ በትብብር ለመስራት ያስችላል- የአገር ሽማግሌዎች


ጅግጅጋ ፤ታህሳስ 25/2016 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ሰነድ በጋራ ትብብር ለመስራት  የሚያስችል መሆኑን የክልሉ አገር ሽማግሌዎች  አስታወቁ ።

ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት መንገድ የሚከፍትላትን የመግባቢያ ስምምነት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድና በሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ መካከል መፈረሙ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የስምምነት ፊርማውን በተመለከተ ያነጋገራቸው የሶማሌ ክልል የሀገር ሽማግሌዎች እንዳሉት የኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ሰነድ በጋራ ትብብር ለመስራት፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ያስችላል።

የኢሳቅ ጎሳ ኢደገሌ ንዑስ ጎሳ ባህላዊ መሪ ሡልጣን አይደሩስ ሙሴ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት የሚያስችላትን ስምምነት በሰጥቶ መቀበል መርህ ስምምነት ላይ መድረሷ ጠቃሚ እርምጃ ነው።

የመግባቢያ ስምምነቱ  በጋራ ትብብር ለመስራትና በጋራ ለማደግ እንደሚቻል የሚያመለክት መሆኑን ተናግረዋል።

ለቀጣናው አገሮች ሰላምና መረጋጋት የሚኖረው ጠቀሜታ የጎላ መሆኑንም አመልክተዋል።

"ስምምነቱንም ሲጠበቅ የነበረና ለቀጣይ ትውልድ ልማት መሰረት የሚጥል" ሲሉ ገልጸውታል።

የመጢጋን ጎሳ ባህላዊ መሪ ሱልጣን ሀሰን ጅብሪል በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያና ሱማሌላንድ ያደረጉት ስምምነት ለቀጣናው መረጋጋትና ለኢኮኖሚያዊ እድገት የሚያደርገው አስተዋጽኦ የላቀ መሆኑን ተናግረዋል።

አልሸባብ ሱማሊያን ሲያጠቃ ኢትዮጵያ ቀድማ በመድረስ ችግሩን መጋፈጧን ያስታወሱት ሱልጣን ሀሰን፤ በዚህም ለሱማሊያ  ሰላምና መረጋጋት ያደረገችው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደነበረ አብራርተዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም