ኢዜአ መረጃን ተደራሽ ከማድረግ ባለፈ ተቋማት የተደራጀ የኮሙኒኬሽን ስርአት እንዲኖራቸው የበኩሉን ሚና እየተወጣ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢዜአ መረጃን ተደራሽ ከማድረግ ባለፈ ተቋማት የተደራጀ የኮሙኒኬሽን ስርአት እንዲኖራቸው የበኩሉን ሚና እየተወጣ ነው
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 25/2016 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት መረጃን ተደራሽ ከማድረግ ባለፈ ተቋማት የተደራጀ የኮሙኒኬሽን ስርአት እንዲኖራቸው የበኩሉን ሚና እየተወጣ መሆኑን የተቋሙ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ነጋሲ አምባዬ ገለፁ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ለ9 የተለያዩ ተቋማት የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ለ30 ቀናት ሲሰጥ የቆየውን ሥልጠና አጠናቋል፡፡
በግራፍክስ ዲዛይን፣ በአኒሜሽን፣ በምስልና ድምፅ ቀረፃ፣ በኤዲቲንግ እና አርካይቭን በተመለከተ ባለሙያዎቹ ስልጠናውን ተከታትለዋል።
በስልጠናው ማጠቃለያ ላይ በመገኘት መልእከት ያስተላለፉት የኢዜአ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ ነጋሲ አምባዬ፤ ተቋሙ መረጃን ተደራሽ ከማድረግ ባሻገር የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎችን በስልጠና በማብቃት የበኩሉን ሚና እየተወጣ ይገኛል፡፡
ለተቋማቱ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች የተሰጠው ስልጠናም የዚሁ አካል መሆኑን ገልጸው ባለሙያዎቹ በስልጠናው ያገኙትን እውቀትና ክህሎት ወደ ተግባር በመቀየር ለተቋማቸው መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
በኢዜአ የስልጠና ምክር እና ምርምር ማዕከል ቡድን መሪ ታደለ ወንድሙ፤ ኢዜአ ለተለያዩ የፌዴራል እና የክልል ተቋማት በሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ የአቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለአንድ ወር ያህል የሰለጠኑት የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችም በግራፍክስ ዲዛይን፣ አኒሜሽን፣ ምስልና ድምፅ ቀረፃ እንዲሁም በኤዲቲንግ እና ሌሎችም መሆኑን ጠቅሰዋል።
የስልጠናው ተሳታፊዎችም በቆይታቸው ጥሩ የሙያ ክህሎትና እውቀት ማግኘታቸውን ገልጸዋል።