ቀጥታ፡

የገበያ ትስስር አለመኖር፣ የምርት ጥራትና ሌሎችም ችግሮች የቆዳና ሌጦ ምርትን ለብክነት እየዳረጉ ነው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 25/2016(ኢዜአ)፦የገበያ ትስስር አለመኖር፣ የምርት ጥራትና ሌሎችም ችግሮች የቆዳና ሌጦ ምርትን ለብክነት እየዳረጉ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎችና የሥራ ኃላፊዎች ተናገሩ።

ኢትዮጵያ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የእንስሳት ኃብት ቢኖራትም የሚገባትን ጥቅም እስካሁን ማግኘት አልቻለችም፡፡

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የቆዳና ሌጦ ምርት በተለይም የበዓል ወቅትን ተንተርሶ የሚሰበሰብ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ሳይሸጥ በየቦታው ሲወድቅ ይስተዋላል።

ከእንስሳት ኃብቶቿ ከሚገኘው ከ30 ሚሊየን በላይ የጥሬ ቆዳና ሌጦ ምርት ውስጥ ከ19 ሚሊየን በላይ የሚሆነው አገልግሎት የማይሰጥ መሆኑንም መረጃዎች ያመለክታሉ።

የቆዳ ኃብት በሚፈለገው ልክ ጥቅም ላይ እንዳይውል ካደረጉት ምክንያቶች መካከልም የቆዳና ሌጦ ዋጋ በዓለም ገበያ መቀዛቀዝ፣  የጥራት ችግርና የገበያ ትስስር አለመኖር ይጠቀሳሉ። 

በተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ችግሮች ምክንያት የቆዳና ሌጦ የጥራት መጓደልም ሌላኛው ምክንያት ተደርጎ ይጠቀሳል።

ከዚሁ ጋር በተገናኘ ኢዜአ ያነጋገራቸው በግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የግብርና ኢኮኖሚክስ ከፍተኛ ተመራማሪ ዶክተር ረሂማ ሙሰማ፤ የኢትዮጵያ ቆዳና ሌጦ ምርቶች በዓለም ገበያ ተፈላጊ ቢሆንም ሀገሪቱ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እያገኘች አይደለም ብለዋል።

ከአርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ የሚሰበሰበው ከ80 በመቶ በላይ የቆዳና ሌጦ ምርት ጥቅም ላይ እየዋለ አለመሆኑንም ገልፀዋል።

በዘርፉ ልማት የገበያ ትስስር አለመኖርና የምርት ጥራት ችግር ከፍተኛ የቆዳና ሌጦ ብክነት እያስከተለ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለዘርፉ ማነቆ የሆኑ ጉዳዮችን በመፈተሽ ዘላቂ መፍትሔ መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል።


 

በአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የቆዳና ቆዳ ውጤቶች ምርምርና ልማት ዴስክ ኃላፊ በለጠ ጸጋዬ፤ የቆዳ ምርት የጥራት መጓደል በጨው መጠን አጠቃቀም ችግርና ሌሎችም ምክንያቶች ኃብቱ ለብልሽት እየተዳረገ መሆኑን ገልፀዋል።

በመሆኑም ዘርፉ ትልቅ የውጭ ምንዛሬ ማግኛና ለበርካታ የሥራ ዕድል የሚፈጥር በመሆኑ በልዩ ትኩረት መሥራት ይገባል ነው ያሉት።


 

የኢንዱስትሪ ግብአቶች ልማት ድርጅት የግዥና ሽያጭ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተወካይ አለማየሁ ወልደዮሐንስ፤ ድርጅቱ ለተመረጡ ኢንዱስትሪዎች ግብአት እያቀረበ መሆኑን ገልፀዋል።

የቆዳ ኢንዱስትሪው ዘርፍም ከተመረጡ ኢንዱስትሪዎች መካከል መሆኑን ገልጸው፤ ለዚሁ ግብአት የሚሆነውን ጨው በማቅረብ ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የጨው አቅርቦትን በተመለከተ 20 የቆዳ ኢንዱስትሪዎች ወርሃዊና ዓመታዊ ፍላጎታቸውን በማቅረብ የሚስተናገዱበት አሠራር ቢኖርም የአቅርቦት እጥረት አለ ብለዋል።


 

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ታረቀኝ ቡሉልታ፤ በቆዳና ሌጦ ገበያ የአሰባሰብ ችግር፣ ዘመናዊ ማቆያ አለመኖሩና ሌሎችም የዘርፉ ችግሮች ናቸው ሲሉ ጠቅሰዋል።

በመሆኑም በቆዳ ልማት ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመለየት ዘላቂ መፍትሔ ለመሻት በመንግሥት የተለያዩ ጥረቶች በመደረግ ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም