ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ለ5ኛ ዙር በከፍተኛ የማዕረግ ሽግግር ያሰለጠናቸውን መኮንኖች አስመረቀ

አዲስ አበባ፤ ታኅሣሥ 25/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ 5ኛ ዙር ከኢንስፔክተር ወደ ዋና ኢንስፔክተር በከፍተኛ የማዕረግ ሽግግር ያሰለጠናቸውን መኮንኖች አስመረቀ።

በምርቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተው ለተመራቂ መኮንኖቹ የስራ መመሪያ የሰጡት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ፖሊስነት ሁሉንም የሰው ልጆች በእኩልነት የሚያገለግል ሙያ እንደሆነ ገልፀዋል።


 

ተመራቂ መኮንኖቹ በቀጣይ የሚሰጣቸውን ተልዕኮ በብቃት በመወጣት ያደገች እና የበለጸገች ሀገር ለመገንባት የበኩላቸውን የአመራርነት ሚና መወጣት እንዳለባቸውም ጠቅሰዋል።

ከማዕረግ ሽግግሩ በተጨማሪ በተመራቂ መኮንኖቹ አነሳሽነት የተሰራውን በኢትዮጵያ የፖሊስ ታሪክ የመጀመሪያው የፖሊስ ሠራዊት አዛዥ የነበሩት እና ለፖሊስ ተቋም ትልቅ መሠረት የጣሉ ብርጋዴን ጀነራል ጽጌ ዲቡ የመታሰቢያ ሐውልት በዩኒቨርሲቲው ዋና ቅጥር ግቢ ተገንብቶ ተመርቋል።

ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል የመታሰቢያ ሐውልቱን በመረቁበት ወቅት ብርጋዴን ጀነራል ጽጌ ዲቡ ታላላቅ ስራዎችን የሰሩ ጠንካራ የፖሊስ መሪ መሆናቸውን ገልፀዋል።


 

ለነገ ትውልድ ታሪክን ለማስተላለፍ የመታሰቢያ ሐውልት ላስገነቡ ተመራቂ መኮንኖች እና ድጋፍ ላደረጉ አካላት ምስጋና ያቀረቡት ኮሚሽነር ጀነራሉ፤ ለብርጋዴን ጀነራል ጽጌ ዲቡ ቤተሰቦችም እንኳን ደስያላችሁ ማለታቸውን ከፌደራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም