ቀጥታ፡

የአብሮነት እሴቶችን በማዳበር በመተጋገዝና በማልማት በጋራ ሀገር ለመገንባት ሁላችንም ልንዘጋጅ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 25/2016(ኢዜአ)፦የአብሮነት እሴቶችን በማዳበር በመተጋገዝና በማልማት በጋራ ሀገር ለመገንባት ሁላችንም ልንዘጋጅ ይገባል ሲሉ የባሕልና ስፖርት ሚኒስትሩ ቀጀላ መርዳሳ ተናገሩ።

በአብሮነት ሳምንት የማጠቃለያ መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ሲሆን በመድረኩ ላይ የተገኙት የባሕልና ስፖርት ሚኒስትሩ ቀጀላ መርዳሳ መልእከት አስተላልፈዋል።


 

በመልዕክታቸውም ህብረ ብሄራዊነት የኢትዮጵያ መለያ የዜጎች ሁሉ የውበትና የሃብት መገለጫ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያዊያን በዘመናት የአብሮነት ጉዞ የባህል፣ የኃይማኖትና ሌሎችም ማህበራዊ መስተጋብሮችን በመወራረስ የጋራ ሃብት በማድረግ እስካሁንም የዘለቁ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያዊያን በአይነተ ብዙ የባህልና ሃይማኖታዊ እሴቶች የታደሉ፣ በአብሮነት፣ በመተጋገዝና በመረዳዳት እንዲሁም በእንግዳ ተቀባይነታቸው የሚታወቁ ስለመሆኑም አንስተዋል። 

የአብሮነት እሴቶችን በማዳበር በመተጋገዝና በማልማት በጋራ ሀገር ለመገንባት ሁላችንም ልንዘጋጅ ይገባል ብለዋል።

የባሕልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ወርቅነሽ ብሩ፤ የአብሮነት ቀን ሚሊየኖች በተሳተፉበት መልኩ በተለያዩ መርሐ ግብሮች መከናወኑን ገልጸዋል።

በቀጣይም አብሮነትን የሚያጠናክሩ ተግባራትን የማከናወን ስራ ቀጣይነት ይኖረዋል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም