አርሶ አደሩ ከኢንዱስትሪዎች ጋር ያለውን ትስስር በማጠናከር የግብዓት አቅርቦት እጥረትን ለማቃለል ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
አርሶ አደሩ ከኢንዱስትሪዎች ጋር ያለውን ትስስር በማጠናከር የግብዓት አቅርቦት እጥረትን ለማቃለል ትኩረት ተሰጥቷል
ሀዋሳ፤ ታህሳስ 25/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪያል ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አርሶ አደሩ ከኢንዱስትሪዎች ጋር ያለውን ትስስር በማጠናከር የግብርና የግብዓት አቅርቦት እጥረትን ለማቃለል ትኩረት መስጠቱን ገለጸ ።
የኮርፖሬሽኑ አመራሮችና በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪያል ፓርክ የሚገኘው የቢራ ብቅል ፋብሪካ ተወካዮች በምዕራብ አርሲ ዞን በአርሶ አደሮች እየለማ ያለውን የቢራ ገብስ ማሳን ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ ወቅት የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪያል ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አክሊሉ ታደሰ እንዳሉት፤ ኮርፖሬሽኑ በባለሀብቶች፣ በአርሶ አደሮችና በአምራች ኢንዱስትሪዎች መካከል ትስስር በመፍጠር የግብዓት አቅርቦት ሂደቱ የተሳለጠ እንዲሆን ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።
“ኮርፖሬሽኑ ሶፍሌት ማልት የተሰኘ በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ውስጥ የቢራ ብቅል በማምረት ተግባር ላይ የተሰማራ ፋብሪካ የቢራ ገብስ በሚፈለገው መጠን ለማግኘት ያስቻለ ትስስር በምዕራብ አርሲ ዞን ከሚገኙ የቢራ ገብስ አምራች አርሶ አደሮች ጋር መፍጠር ተችሏል” ብለዋል።
አርሶ አደሮቹ የሚያመርቱትን የቢራ ገብስ ያለ ደላላ ጣልቃ ገብነት በተመረጡ ሞዴል አርሶ አደሮች በኩል ለፋብሪካው በማቅረብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረጉን ጠቁመዋል።
በዚህም ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ በመተካትና ወደ ውጪ የሚላኩትን መጠን በማሳደግ የውጪ ምንዛሪን ለማግኘት እንዲቻል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከውጪ የሚገባውን የቢራ ብቅል ሙሉ በሙሉ በማስቀረት በአገር ውስጥ ተመርቶ ለሁሉም ቢራ ፋብሪካዎች እንዲቀርብ መደረጉን ገልጸዋል።
ትስስሩ አርሶ አደሩ ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ የቢራ ገብስ ምርጥ ዝርያዎችን በባለሀብትና በተመረጡ ሞዴል አርሶ አደሮች በማባዛት የቢራ ገብስ ለሚያመርቱ 60 ሺህ አባላት በኦሮሚያ ክልል ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ በኩል እንዲደርሳቸው ይደረጋል ነው ያሉት።
“ኩባንያው ሁለተኛ ዙር የማስፋፊያ ስራ እያከናወነ ነው” ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ “በአውሮፓና አሜሪካ የሚገኙ መሰል የብቅል አምራች ኢንዱስትሪዎች የብቅል ፋብሪካ ለመገንባት ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል።
በሶፍሌት ማልት የአቅርቦት ሰንሰለት ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ በዳዳ የሱፍሌት ማልት የቢራ ብቅል ፋብሪካ ብቅል አምርቶ ለቢራ ፋብሪካዎች የማቅረብ ስራውን ከሶስት አመት በፊት እንደጀመረ ተናግረዋል።
ለፋብሪካዎች የሚያቀርበውን የቢራ ብቅል ያለመቆራረጥ ለማቅረብና ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት ታስቦ አርሶ አደሩ የቢራ ገብስ እንዲያመርት እየተደረገ ነው ያሉት።
የምዕራብ አርሲ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ይሳቅ ገመዳ እንዳሉት፤ በዞኑ የቢራ ገብስ አምራች አርሶ አደሮችን ቁጥር በማሳደግ በሀገሪቱ ለሚገኙ ተጠቃሚዎች እንዲያቀርቡ መምሪያው ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው።
በዞኑ አርሶ አደሮች ያመረቱትን ምርት ከራሳቸው በመረከብ ለኢንዱስትሪያል ፓርኮች በቀጥታ ማቅረብ እንዲችል ከሱፍሌት ማልት ጋር የተፈጠረው ትስስር ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።
የምርጥ ዘር አቅርቦቱ ከኦሮሚያ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ ጋር በመሆን ተበጥሮ የተዘጋጀ ምርት በቀጣይ አመት ለአርሶ አደሩ እንደሚቀርብ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ኢንደስትሪያል ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አክሊሉ ታደሰ የተመራው ቡድን በምዕራብ አርሲ ዞን ሻሸመኔ ዙሪያና ቆሬ ወረዳ በአርሶ አደሮች ማሳ እየለማ ያለ የቢራ ገብስና ምርጥ ዘርን ተዘዋውሮ ጎብኝቷል።