ባለፉት አምስት ወራት በሐሰተኛ ደረሰኝ ሊወራረድ የነበረ 530 ሚሊዮን ብር ማዳን ተችሏል

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 25/2016(ኢዜአ)፦የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ባለፉት አምስት ወራት በሐሰተኛ ደረሰኝ ሊወራረድ የነበረ 530 ሚሊዮን ብር ማዳን መቻሉን አስታውቋል።

የቢሮው የህግ ተገዥነት ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ኮማንደር አሕመድ መሐመድ ቢሮው በታክስ አሰባሰብ ላይ የሚስተዋሉ ህገወጥ አሰራሮችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህን ተከትሎ ባለፉት አምስት ወራት በጥናት ላይ የተመሰረተ ኦፕሬሽን በማካሄድ በሐሰተኛ ደረሰኝና ያለ ደረሰኝ ግብይት በፈፅሙ ነጋዴዎች እና ድርጅቶች ላይ እርምጃ መወሰዱን ገልፀዋል።

በዚህም ቢሮው ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጋር በመቀናጀት በሐሰተኛ ደረሰኝና ያለ ደረሰኝ ግብይት ሲፈፅሙ በተገኙ 572 ድርጅቶች ላይ ህጋዊ እና አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰዱን ኮማንደር አሕመድ ተናግረዋል።

ከአዲስ አበባ ወደ ክልል ከተሞች የተለያዩ ሸቀጦችን ጭነው በሚያጓጉዙ 193 ተሽከርካሪዎች ላይ  በተደረገ የደረሰኝ ቁጥጥር 70 ሚሊዮን ብር ማዳን መቻሉን አስታውቀዋል።

በአምስት ወራት ውስጥ በ6 ሺ 887 አጠራጣሪ ደረሰኞች ላይ ማጣራት በማድረግ 1 ሺህ 997 ደረሰኞች ሐሰተኛ ሆነው መገኘታቸውን አብራርተዋል፡፡

በዚህም በህገ ወጥ መንገድ ሊወራረድ የነበረ 530 ሚሊየን ብር በወጪ እንዳይወራረድ እና ተመላሽ እንዳይጠየቅበት መደረጉን ተናግረዋል።

ሀሰተኛ ደረሰኝና መሰል የማጭበርበሪያ ስልቶችን በመጠቀም መንግስት ማግኘት ያለበትን ገቢ የሚያሳጡ አዝማሚያዎች በመጨመራቸው በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በህገ ወጥ ተግባሩ እየተሳተፉ ያሉ ግብር ከፋዮች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ኮማንደር አሕመድ አሳስበዋል፡፡

ህብረተሰቡም ጥቆማ በመስጠት የበኩሉን ኃላፊነት እንዲወጣ በዚሁ ወቅት ጥሪ አቅርበዋል፡፡
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም