ለገናና ጥምቀት በዓላት የምርት እጥረት እንዳይፈጠር በቂ ዝግጅት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
ለገናና ጥምቀት በዓላት የምርት እጥረት እንዳይፈጠር በቂ ዝግጅት ተደርጓል
አዲስ አበባ፤ታህሳስ 25/2016(ኢዜአ)፦ ለገናና ጥምቀት በዓላት ላይ የምርት እጥረት እንዳይፈጠር በቂ ዝግጅት መደረጉን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ መጪው የገናና ጥምቀት በዓላት የምርት አቅርቦትን በተመለከተ መግለጫ ሰጥቷል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ፍስሐ ይታገሱ እንደገለጹት፤ ሚኒስቴሩ በበዓላቱ ወቅት የምርት እጥረት እንዳይፈጠር በቂ ዝግጅት አድርጓል ብለዋል።
በተለይ ሰው ሠራሽ የምርት እጥረትን ለመከላከል ''ከፌደራል የዋጋ ማረጋጋትና ሕገ-ወጥ ንግድ ግብረ-ኃይል'' ጋር በመተባበር በርካታ ተግባራትን ማከናወኑን ተናግረዋል።
በበዓላቱ የምግብ ፍጆታዎች፣ የግብርና ምርቶች እንዲሁም ለእርድ የሚውሉ የቁም እንስሳትና የእንስሳት ተዋፅዖ ቀርበዋል ብለዋል።
እንደ ሀገር በተቋቋሙ 856 የቅዳሜ እና እሁድ ገበያዎች ለበዓል አስፈላጊ የሆኑ ምርቶችን ጨምሮ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች እየተሸጡ መሆኑንም አንስተዋል።
ከ18 ሚሊየን ሊትር የሚበልጥ ዘይት፣ ከ8 ሚሊየን በላይ እንቁላል 3 ነጥብ 2 ሚሊየን ኩንታል ስኳርና ሌሎች ምርቶችም መቅረባቸውን ተናግረዋል።
እንዲሁም 600 ሺህ በግና ፍየል፣ ከ500 ሺህ በላይ ሰንጋዎች ለበዓላቱ የቀረቡ ሲሆን፤ በአዲስ አበባና በክልሎች ከሚያሠራጩ የአካባቢው አቅራቢዎች ጋር ትስስር መፈጠሩን ገልፀዋል።
ከባለ ድርሻ አካላትም ከ3ሺህ ኩንታል በላይ የስንዴ ዱቄት፣ ፓስታና ማካሮኒ በብዛት ወደ ገበያ መግባታቸውን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።