ቀጥታ፡

በሃይማኖታዊ በዓላትና ስብስቦች ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው መልዕክቶች ሊተላለፍባቸው አይገባም- የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ

አዲስ አበባ፤ታህሳስ 25/2016(ኢዜአ)፦ ሃይማኖታዊ ክበረ በዓላትና ስብስቦች የመንፈሳዊ ልዕልና መገለጫ መድረኮች እንጂ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው መልዕክቶች ሊተላለፍባቸው አይገባም ሲል የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ገለጸ።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ወቅታዊ ሁኔታዎችን በተመለከተ መግለጫ አውጥቷል።

በመግለጫውም “ሃይማኖታዊ ክበረ በዓላትና ስብስቦች የመንፈሳዊ ልዕልና መገለጫ መድረኮች እንጂ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው መልዕክቶች ሊተላለፍባቸው አይገባም” ሲል አሳስቧል፡፡

ሃይማኖቶች የመንፈሳዊ እና ማኅበራዊ ዕሴት መሠረቶች በመሆን ከፍተኛ የሆነ የሥነ ምግባርና የግብረ ገብነት ትምህርትና ግንባታ የሚከናወንባቸው ማዕከላት መሆናቸውን ያመለከተው መግለጫው የሰዎችን ማኅበራዊ ግንኙነትና ቁርኝነትን በማጠናከር ሰላም፣ መከባበር፣ አብሮነት፣ ይቅርታ፣ እርቅ፣ ፍትህ እና የመሳሰሉ በጎ ዕሴቶችን በማስተማር ዘመናትን የዘለቀ አገልገሎት ሲሠጡ ኑረዋል ብሏል።

ይህም አገራዊ አንድነትን አስጠብቆ ለመዝለቅ አስችሏል ሲል አጽንኦት የሰጠው መግለጫው የሃይማኖት አባቶች ዋና ተልዕኳቸውና አገልግሎታቸው ሰዎችፈሪሀ ፈጣሪ አድሮባቸው የመንፈሳዊ ልዕልና እንዲጎናፀፉ ማድረግ ሲሆን ለዚህም ራሳቸውን ከዓለማዊ ጉዳዮችና ጣጣዎች በመራቅ እውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወት በምሳሌነት እየኖሩ አስተምህሮው የሚያዛቸውን በተግባር ገልጠዋል ሲልም አመልክቷል፡፡

በተለይም በመንግስታዊም ይሁን መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት የሚስተዋሉ በደሎችንና ኢፍትሐዊነቶች ሁሉ እንዲታረሙና እንዲስተካከሉ መጣር፣ አጥፊዎችም ከስህተታቸው እንዲታረሙ በፍቅር መገሰፅ ሃይማኖታዊና የተለመደ አሠራር በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል እንላለን ነው ያለው፡፡

መግለጫው አክሎም ይሁን እንጅ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንዳንድ የሃይማኖት አባቶች ከዚህ መሠረታዊ ተልዕኮና ዓላማ በማይስማማ አኳኋን ለሃይማኖታዊ ተግባርና ዓላማ በሚደረጉ ስብስቦች እና በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያ በኩል ተገቢ ያልሆኑና በአብዛኛው ፖለቲካዊ ይዘት የጎላባቸው፣ አገር አፍራሽና ደም አፋሳሽ ስብከቶችና ትንታኔዎች ሲነገሩ እንመለከታለን ብሏል፡፡

ስብከቶቹና ንግግሮቹ ፖለቲካውና ፖለቲከኞችን የሚተቹ ወይም የሚደግፉ ከመሆናቸው በላይ አንዱ በአንዱ ላይ እንዲነሳ የመቀስቀስና የማነሳሳት አዝማሚያ የሚታይባቸው መሆኑ ጉዳዩ ከየትኛው ሃይማኖታዊ አስተምህሮ ጋር የማይስማማና ድጋፍም የሌለው መሆኑ ደግሞ የስብከት ልምምዱ አደገኛና በእጅጉ አሳሳቢ እንዲሆን ያደርገዋል ሲል አምልክቷል ጉባኤው በመግለጫው።

እንዲህ ዓይነቱ ስብከትና አካሄድም የሰላም፣ የመከባበርና የአብሮነት ዕሴቱን የሚጎዳ በመሆኑ በአፋጣኝ ሊታረም ይገባል ነው ያለው ጉባኤው።

በዚህም የሃይማኖት ተቋማትም እንዲህ ዓይነት ስብከት የሚሠብኩና የሚናገሩ አባቶችን፣ አስተማሪዎችን ወይም ሰባኪ አገልጋዮችን እንዲታረሙ የማድረግ ተቋማዊ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ መንፈሳዊ ልዕልናን እንዲያሰፍኑ ጭምር ጉባኤያችን በአጽንኦት ያሳስባል ሲል በመግለጫው አስታውቋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም