በጣሊያን እና ጀርመን የሚኖሩ ወገኖች በሁለተኛው ትውልድ ጥሪ ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ከፍተኛ ፍላጎት እያሳዩ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጣሊያን እና ጀርመን የሚኖሩ ወገኖች በሁለተኛው ትውልድ ጥሪ ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ከፍተኛ ፍላጎት እያሳዩ ነው
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 25/2016 (ኢዜአ)፦በጣሊያን እና ጀርመን የሚኖሩ ወገኖች በሁለተኛው ትውልድ ጥሪ ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ከፍተኛ ፍላጎትና ዝግጁነት ማሳየታቸውን በየአገራቱ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች አስታወቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ወደ መነሻችሁ ተመለሱ “Back to Your Origins” በሚል በውጭ አገራት የተወለዱ ወገኖች ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወቃል።
በተለያዩ የዓለም አገራት የሚኖሩ ሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያን በአካል ተገኝተው በማየት ሁለንተናዊ ግንዛቤና አጠቃላይ ያላትን ትሩፋት እንዲያጤኑ ለማስቻል ግብዣው ትልቅ ትርጉም ያለው ነው።
ጥሪው Connect to Your Multi-Cultural Roots (ከብዝኃ ባህል መሰረት ጋር መገናኘት) በሚል የመጀመሪያው ዙር ከታህሳስ 20 እስከ ጥር 30 ቀን 2016 ዓ.ም የሚካሄድ መሆኑን የወጣው መርሃ ግብር ያመለክታል።
Connect to Your Historical Roots (ታሪካዊ መሰረትዎን ይወቁ) የተሰኘው ሁለተኛው ዙር ደግሞ ከየካቲት 20 እስከ ሚያዝያ 30 ቀን 2016 ዓ.ም የሚካሄድ ይሆናል።
አሻራዎን ያኑሩ፣ የእረፍት ጊዜዎን ያጣጥሙ (Leave your Legacy, savor your holiday) የተሰኘው ሶስተኛው ዙርም ከሰኔ 10 ቀን 2016 ዓ.ም እስከ መስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም ይካሄዳል።
በመሆኑም በእነዚህ መርሃ ግብሮች ላይ በመታደም ኢትዮጵያን ለማየት በተለያዩ የዓለም አገራት የሚኖሩ ሁለተኛው ትውልድ ዳያስፖራዎች ወደ መነሻቸው እያማተሩ ነው።
ከዚሁ ጋር በተገናኘ በጣሊያን እና ጀርመን እየተደረገ ያለውን ዝግጅት በማስመልከት ኢዜአ በየአገራቱ የሚገኙ የኢትዮጵያን ኢምባሲዎች አነጋግሯል።
በጣሊያን የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሚቱ ሃምቢሳ፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ጥሪን ተከትሎ ኢምባሲው ኮሚቴ በማቋቋም እቅድ አውጥቶ የማስተባበርና መረጃዎችን የማድረስ ስራ እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
በዚህም ኤምባሲው በሚከታተላቸው አገራት በጣሊያን፣ ግሪክና ማልታ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ተከታታይ ውይይት መደረጉን ጠቁመዋል።
በተመሳሳይ በኤምባሲው ድረ-ገጽ ጥሪውን በማስተላለፍና ከዲያስፖራ ማህበረሰብ ጋር በበይነመረብ የጥሪው አስፈላጊነት ላይ ውይይት መደረጉን አብራርተዋል።
ወላጆች ልጆቻቸውን እንዲያስመዘግቡና ልጆቻቸውን ይዘው መሄድ ከፈለጉ መርሃ ግብር መኖሩን የማስተዋወቅ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የተደረገው ጥሪ በውጭ አገራት የተወለዱ ወገኖች የኢትዮጵያን ታሪክ በቅጡ እንዲያውቁ፣ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችን እንዲጎበኙና አሻራቸውንም ማኖር እንዲችሉ ጥሩ አጋጣሚ የፈጠረ በመሆኑ በርካቶች ደስታቸውን ገልጸዋል ብለዋል አምባሳደሯ።
በወጣው መርሃ ግብር መሰረትም ወደ ኢትዮጵያ ለማምራት በርካቶች ከፍተኛ ፍላጎትና ተነሳሽነት አሳይተዋል ነው ያሉት።
በአንደኛና ሁለተኛው ዙር ጥሪ በተለይም በስራ ዓለም ላይ ያሉ ወጣቶች ለመታደም ከፍተኛ ፍላጎት እያሳዩ ሲሆን በሶስተኛው ዙርም በትምህርት ላይ ያሉ ታዳጊዎች ለመገኘት ፍላጎታቸውን እየገለጹ ነው ብለዋል።
በጀርመን የኢትዮጵያ ኤምባሲ የዲያስፖራ ዘርፍ አስተባባሪ አስቻለው ከበደ በበኩላቸው፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ጥሪ በብዙዎች ዘንድ ደስታን የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም ኢምባሲው የጥሪውን ይዘትና አላማ የማስተዋወቅ ስራና አስተባበሪ ኮሚቴ በማዋቀርም የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
በጀርመን የበርካታ ዳያስፖራ እንቅስቃሴ የሚደረግበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ፍላጎትና ተነሳሽነት መኖሩን ጠቅሰው ወቅቱ የትምህርት የእረፍት ጊዜ በመሆኑ በመጀመሪያው ዙር ጥሪ ኤምባሲው ባዘጋጀው የመመዝገቢያ ሊንክ መሰረት እየተመዘገቡ ይገኛሉ።
በሁለተኛው ዙር ለሚሄዱትም ዝግጅት መረጃ የማድረስ ስራ እየተሰራ ሲሆን ሶስተኛው ዙር ጥሪ በተደረገበት ወቅት በጀርመን የክረምት ወቅት በመሆኑ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ዳያስፖራ የመታደም ፍላጎት መኖሩን ተናግረዋል።
በጀርመን የሚገኙ በርካታ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያን በተለያዩ አጋጣሚዎች በሀገራቸው ሁለንተናዊ ተሳትፎ ማድረጋቸውንም አስታውሰዋል።
በተለይም በልማትና ኢንቨስትመንት በመሳተፍና በእውቀት ሽግግርና ሌሎችም ሀገራዊ ጥሪዎች እየተሳተፉ መሆኑን ጠቅሰው ሌሎችም በቀጣይ የመሳተፍ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሁለተኛው ትውልድ ጥሪም የኢትዮጵያን ታሪክ፣ የልማት እንቅስቃሴና ሌሎችም ሀገራዊ እሴቶች በቅጡ ለመረዳት የተዘጋጁበት ልዩ አጋጣሚ መሆኑን የዘርፉ አስተባበሪ ተናግረዋል።
በእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር በሀገር ቤት ለሚገኙ ወጣቶች ለማጋራትም መልካም አጋጣሚ መሆኑን ጠቅሰው በገበታ ለትውልድ የለሙና ሌሎችንም የልማት እንቅስቃሴዎች በመጎብኘት ኢትዮጵያን በቅጡ አውቆ ለማሳወቅ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም በጀርመንና አካባቢው የሚኖሩ ዳያስፖራዎች የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተቀብለው ልጆቻቸውን እንዲያስመዘግቡ፣ እንዲልኩና ራሳቸውም እንዲታደሙ ኤምባሴው ጥሪ አቅርቧል።
በጀርመን የኢትዮጵያ ኤምባሲ የኢትዮጵያውያን መብት እንዲከበር በማድርግ፣ በልማትና ኢንቨስትመንት ኢንዲሳተፉ፣ በእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዙሪያ ሰፊ ጥረት እያደረገ መሆኑ ታውቋል።