የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እስከሚጠናቀቅ ድጋፋችንን እንቀጥላለን -- ምእራብ ሸዋ ዞን ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እስከሚጠናቀቅ ድጋፋችንን እንቀጥላለን -- ምእራብ ሸዋ ዞን ነዋሪዎች
አምቦ፤ታህሳስ 25 /2016 (ኢዜአ)፡- የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ቀሪ ስራን ለማጠናቀቅ ቦንድ በመግዛት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በምእራብ ሸዋ ዞን የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ፡፡
ለአንድ ወር በተካሄደው የቦንድ ሽያጭ ከ43 ሚሊዬን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የዞኑ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የመንግስት ሰራተኛ የሆኑት አቶ ሙላቱ ተስፋዬ ፤ ''ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሁላችንም የወደፊት ተስፋ ነው'' ብለዋል።
''ከማገኘው አነስተኛ ደምወዝ ለግድቡ ድጋፍ የአንድ ሺህ ብር ቦንድ ገዝቻለሁ'' ያሉ ሲሆን የግድቡ ግንባታ ቀሪ ስራን ለማጠናቀቅ ቦንድ በመግዛት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡
ሌላዋ የመንግስት ሰራተኛ ወይዘሮ ሙሉእመቤት ተሾመ በበኩላቸው፤ ''ታላቁ የህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያዊያን ከድህነት ለመውጣት ተስፋ አድርገን በተባበረ አቅም እየገነባነው እንገኛለን ''ብለዋል፡፡
የግድቡ ቀሪ የግንባታ ሂደት እስከሚጠናቀቅ የጀመሩትን ድጋፍ እንደሚቀጥሉ አስረድተዋል።
በተሰማራበት አነስተኛ የንግድ ስራ ከሚያገኘው ገቢ የሁለት ሺህ ብር ቦንድ መግዛቱን የገለጸው ደግሞ የአምቦ ከተማ ነዋሪ አቶ ሙስጠፋ መሃመድ ሲሆን የግድቡ ግንባታ አስኪጠናቀቅ የቦንድ ግዥ በመፈጸም ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግሯል።
የዞኑ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ ወርቅነህ ሁንዴሳ ለኢዜአ እንዳስታወቁት የዞኑ ሕዝብ ለግድቡ ግንባታ በቦንድ ግዥና በስጦታ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
በተያዘው ዓመት በዞኑ 45 ሚሊዬን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ከታህሳስ 3 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በተደረገ እንቅስቃሴ ከ43 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያለው ቦንድ በመሸጥ የዓመቱ እቅድ 95 ነጥብ 61 ከመቶ መከናወኑን ገልጸዋል፡፡
በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች እየተካሄደ በሚገኘው የቦንድ ግዢ የመንግስት ሰራተኞች፣ ወጣቶች፣ ነጋዴዎች፣ ባለሃብቶች፣ የመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የዞኑ ህብረተሰብ ክፍሎች በንቃት እየተሳተፉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የምዕራብ ሸዋ ዞን የመንግሥት ሠራተኞች፣ ባለሀብቶች፣ አርሶ አደሮችና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች እስካሁን ለታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከቦንድ ሽያጭና በስጦታ ከ145 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር በላይ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን የጽህፈት ቤቱ መረጃ ያመለክታል።