የስዕል ማራቶን ክብረ ወሰንን የሰበረው ናይጄሪያዊ የሥነ ጥበብ ተማሪ

326

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 25/2016(ኢዜአ)፡- ለተከታታይ 100 ሰዓታት የተለያዩ ስዕሎችን የሳለው ናይጄሪያዊው የሥነ ጥበብ ተማሪ የአለም የስዕል ማራቶን ክብረ ወሰንን ሰብሯል።

በአሜሪካ ጆርጂያ ግዛት በሳቫና የስዕልና ዲዛይን ኮሌጅ ተማሪ የሆነው ቻንስለር አሀጎቱ ለረጅም ሰዓታት በመሳል የአለም ክብረ ወሰንን እንደጨበጠ ጊነስ ወርልድ ሪከርድስ አስታውቋል።

ከዚህ ቀደም እ.አ.አ በ2013 በቤልጄየማዊው የስነ ጥበብ ተማሪ ሮናልድ ፓልሜርትስ የተያዘውን ለ60 ሰዓት የመሳል ክብረ ወሰን በመስበር ነው እውቅናውን የጨበጠው።

ለአራት ቀናት ገደማ ቻንስለር ባካሄደው የስዕል ስራ የታዋቂ ሰዎችን ጨምሮ፣ ምግቦች፣ ዕጽዋትና እንሰሳት እንዲሁም 106 ልዩ ልዩ ስዕሎች መሳሉን ዘገባው አመልክቷል።

ለተከታተይ 88 ሰዓታት በስዕል ስራው ላይ ከቆየ በኋላ የድካም ስሜት ታይቶበት ነበረ ያለው ዘገባው ድካሙን በማሸነፍ ክብረ ወሰኑን መስበሩን አስነብቧል።

ቻንስለር አሀጎቱ እውቅናውን ተከትሎ በሰጠው አስተያየት “ወደ ስነ ጥበብ ትምህርት ቤት የመጣሁት ሕልሜን እውን ለማድረግ ነው፣ ለ100 ሰዓታት ያለ እረፍት በመሳል ያሳካሁት ድል ነው ብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም