ተቋማዊ አደረጃጀትንና ቅንጅታዊ ሥራን በማጠናከር ለህብረተሰብ አደጋ የሆኑ የጤና ሥጋቶችን ቀድሞ መከላከል ይገባል--ዶክተር ሊያ ታደሰ - ኢዜአ አማርኛ
ተቋማዊ አደረጃጀትንና ቅንጅታዊ ሥራን በማጠናከር ለህብረተሰብ አደጋ የሆኑ የጤና ሥጋቶችን ቀድሞ መከላከል ይገባል--ዶክተር ሊያ ታደሰ
ሰመራ ፤ ታህሳስ 24/2016 (ኢዜአ)፦ ተቋማዊ አደረጃጀትንና ቅንጅታዊ ሥራን በማጠናከር እና ትክክለኛ መረጃ ላይ በመመስረት ለህብረተሰብ አደጋ የሆኑ የጤና ሥጋቶችን ቀድሞ መከላከል እንደሚገባ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ።
ላለፉት ሦስት ቀናት በሰመራ ሎጊያ ከተማ የተካሄደው የህብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ፎረም ተጠናቋል።
በፎረሙ ማጠቃለያ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ባለፉት ዓመታት እንደ ጎርፍና ወረርሽኝ በተከሰቱ ጊዜ ከተቋማት ጋር በትብብርና በቅንጅት የተሰሩት ሥራዎች አበረታች ናቸው።
ተቋማዊ የሆኑ አደረጃጀቶችንና ቅንጅታዊ ሥራዎችን በማጠናከር እና በትክክለኛ መረጃ ላይ በመመስረት የህብረተሰብ የጤና ሥጋቶችን ቀድሞ መከላከል እንደሚገባ ገልጸዋል።
መልካም ተሞክሮዎችን በመውሰድና በትብብር በመስራት ለህብረተሰብ አደጋ የሆኑ የጤና ስጋቶችን አስቀድሞ ለመከላከል በሚደረገው ጥረት አመራሩ በትኩረት እንዲሰራም አስገንዝበዋል።
እንደ ኮሌራ ያለ ወረርሽኝ ሲከሰት ፈጥኖ ለመቆጣጠር በየደረጃው ያለው አመራር በቁርጠኝነትና በኀላፊነት ስሜት ሊሰራ እንደሚገባም ነው ዶክተር ሊያ ያመለከቱት።
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዮት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ሀይሉ በበኩላቸው ተቋሙ ላለፉት ዓመታት በዝግጁነት፣ በቅድመ ማስጠንቀቂያ እና በተጋላጭነት ስጋት ዳሰሳ ትንበያ ላይ ሥራዎችን ሲሰራ መቆየቱን ጠቁመው፣ በቀጣይም ይሄ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ድንበር ተሻጋሪ በሽታዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተቋማት አደረጃጀቶችና አስራሮች በተለያዮ ድጋፎች እንዲጠናከሩ የማድረግ ሥራ መከናወኑንም ተናግረዋል።
የምርምር መረጃ ትንተና ልየታ ሥራን በማጠናከር፣ የላቦራቶሪ አቅምን በማሳደግ እና በአቅም ግንባታ ስራዎች የህብረተሰብ ጤና ስጋቶችን ቀድሞ ለመከላከል የተጀመረው ሥራ እንደሚጠናከርም ዶክተር መሳይ አመልክተዋል።