ቀጥታ፡

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለዲፕሎማቲክ ማኀበረሰብ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ ተሰጠ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 24/2016 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እና ሶማሌላንድ መካከል የተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ በሚመለከት መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የዲፕሎማቲክ ማኀበረሰብ አባላት ገለጻ ተደርጓል። 


 

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ሚኒስትር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን አዲስ የተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ ኢትዮጵያ የባህር በር እና የወደብ አማራጮችን የሚያሰፋ እንደሆነ ገልጸዋል። 

አምባሳደር ሬድዋን ሰነዱ ኢትዮጵያ በቀጠናው ሰላም እና ደህንነት ከማስጠበቅ አንጻር ትልቅ ሚና እንዳለው እና ይህም የራሳችንን ህልውና የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል። 

የፍትህ ሚኒስትር ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ በበኩላቸው የመግባቢያ ሰነዱ ለኢትዮጵያ የባህር በር እና ወደብ የሚያስገኝ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ እና ሶማሌላንድ መካከል በንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ በቴክኖሎጂ፣ በግብርና እና በቱሪዝም ትብብር እና አጋርነት የሚያካትት መሆኑን አስረድተዋል። 

የጠቅላይ ሚንስትሩ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አማካሪ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ በሰላም መንገድ የባህር በር እና የወደብ ባለቤት መሆን እንደሚቻል አሳይታለች።

 ኢትዮጵያ እና ሶማሌላንድ ከተፈራረሙት የመግባቢያ ሰነድ ጋር በተያያዘ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሰራተኞች እና ለተጠሪ ተቋማት በትላንትናው ዕለት ገለጻ ተሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም