ቀጥታ፡

አገልግሎቱ የትምህርት ማስረጃና ሌሎችም አገልግሎቶችን በኦንላይን እየሰጠ ነው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 24/2016 (ኢዜአ)፦ የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች አገልግሎት፤ ለተገልጋዮች የትምህርት ማስረጃና ሌሎችም አገልግሎቶችን በኦንላይን እየሰጠ መሆኑን አስታወቀ።

የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት የትምህርት ማስረጃና የፈተና አስተዳደር ስራዎችን ለማዘመን የተሰሩ ሥራዎችን አስመልከቶ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥቷል።

የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር እሸቱ ከበደ፤ በርካታ ዜጎች ከትምህርት ማስረጃ ጋር በተያያዘ ጥያቄ ለማቅረብ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍል ወደ ተቋሙ እንደሚመጡ ገልጸዋል።

ከትምህርት ማስረጃ ብልሽት፣ መጥፋት፣ የስም ግድፈት፣ የመረጃ ትክክለኝነት እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ጥያቄ የሚያቀርቡ ዜጎች ለእንግልት እና ላልተገባ ወጪ ሲዳረጉ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

በመሆኑም ተገልጋዮች የሚያጋጥማቸውን ውጣ ውረድ ታሳቢ በማድረግ ከ2015 በጀት ዓመት ጀምሮ አሰራሮችን ለማዘመን አገልግሎቱ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህም ውስጥ አገልግሎት ፈላጊዎች በበይነ-መረብ እና በፖስታ የሚስተናገዱበት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን አስረድተዋል።

በበይነ-መረብና የፖለስታ አገልግሎት አማራጮች የትምህርት ማስረጃ የማጣራት፣ ወደ ሌላ ተቋም የመላክ፣ ሰርተፊኬት የመስጠትና ማስረጃን የማረጋገጥ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚህም የተገልጋዮችን ውጣ ውረድ በማስቀረት ባሉበት ሆነው ቀልጣፋና ወጪን በቀነሰ መልኩ አገልግሎት እያገኙ መሆኑን ገልጸዋል።

የተፈታኝ ምዝገባን ጨምሮ የፈታኝና ፈተና አስፈፃሚ ምልመላ፣ ድልድልና ስምሪቶችንም በበይነ-መረብ ለማካሄድ የሚያስችል አሰራር ተፈጥሯል ብለዋል።

በመሆኑም አገልግሎት ፈላጊዎች በኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎትና በተቋሙ የበይነ-መረብ አገልግሎት https://services.eaes.et በማመልከት መገልገል ይችላሉ ብለዋል። 

የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ ሃና አርዓያ-ስላሴ፤ ድርጅቱ በኢትዮጵያ ከ700 እና በሌሎች ዓለማት 180 በላይ ባሉት ቅርንጫፎች የአገልግሎት አድማሱን እያሰፋ ነው ብለዋል።

ከትምህርት ማስረጃ ጋር በተያያዘ አገልግሎት የሚፈልጉ ሰዎችም በአቅራቢያ በሚገኝ ቅርንጫፍ አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ የተቋሙን የአሰራር ማሻሻያ እያገዘ መሆኑን ገልጸዋል።

 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም