ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር ያደረገችው ስምምነት የጋራ ተጠቃሚነት መርህን የተከተለ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር ያደረገችው ስምምነት የጋራ ተጠቃሚነት መርህን የተከተለ ነው
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 24/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር ያደረገችው የባህር በር አጠቃቀም ስምምነት አዎንታዊና ለተቀሩት የአካባቢው ሃገራት የሚተርፍ ነው ሲሉ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ ተናገሩ ።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያ የሆኑት አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ ከቢቢሲ 'ፎከስ ኦን አፍርካ'ጋር ባደረጉት ቆይታ ኢትዮጵያ ካላት የመልማት አቅምና የምጣኔ ሃብት እድገት አንጻር ተጨማሪ የባህር በሮች እንደሚያስፈልጋት ገልጸዋል
አቶ ዘመዴነህ ላለፉት ሰላሳ አመታት ኢትዮጵያ የባህር በር ሳይኖራት መቆየቷን አስታወሰው ከሰሃራ በታች ከደቡብ አፍሪካና ከናይጄሪያ ቀጥሎ 3ኛውን ግዙፍ የምጣኔ ሃብት የገነባችው ኢትዮጵያ የባህር በር ፍላጎቷን ይፋ ብታደርግ የሚገርም ሊሆን አይገባም ብለዋል።
ዛሬ ያለውን ብቻም ሳይሆን የወደፊቶቹን በርካታ አስርት አመታት የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገት ታሳቢ ተደርጎ ወደ ስምምነቱ መገባቱን በመግለጽ ኢትዮጵያ በአለም ካሉ 15 ባለግዙፍ ኢኮኖሚ ሃገራት መካከል አንዷ እንደምትሆን በርካታ ማሳያዎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
ሃገራት የባህር በሮችን ከሌሎች ሃገሮች ለረጅም ጊዜ በሚቆይ ስምምነት መከራየታቸው አዲስ አይደለም ያሉት አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ አሜሪካም የፓናማ መተላለፊያን በአንድ መቶ አመታት ኪራይ ውል ስትጠቀመበት እንደነበር አስታውሰዋል።
ጉዳዩ በአካባቢው ያሉ ሃገራትን እንደሚጠቅም ነጋሪ የሚያስፈልገው አለመሆኑን ጠቅሰው በዚህ ስምምነት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ብቻውን ከ3 እስከ 5 በመቶ እድገት ሊያሳይ እንደሚችል አመላካቾች መኖራቸውንም አክለው አመልክተዋል።