ቀጥታ፡

በሚቀጥሉት አስር ቀናት የሚኖረው የአየር ሁኔታ ለድኅረ ሰብል ስብሰባ እንቅስቃሴ አመቺ  ሁኔታን ይፈጥራል  

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 24/2016 (ኢዜአ)፦ በሚቀጥሉት አስር ቀናት የሚኖረው የአየር ሁኔታ ለድኅረ ሰብል ስብሰባ እንቅስቃሴ አመቺ ሁኔታን እንደሚፈጥር የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለፀ።

ኢንስቲትዩቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ፤ በሚቀጥሉት አስር ቀናት የሚኖረው የአየር ሁኔታ በመካሔድ ላይ ላለው የድኅረ ሰብል ስብሰባ እንቅስቃሴ አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል ብሏል። 

በተለይም በደቡብ አጋማሽና በመካከለኛው የአገሪቱ ክፍሎች ላይ የሚኖረው እርጥበት ዘግይተው ለተዘሩ ሰብሎችና ለቋሚ ተክሎች የውኃ ፍላጎት ለማሟላት እንደሚረዳ ተጠቁሟል። 

እርጥበቱ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው ለሆኑት ጥምር ግብርና ለሚያካሂዱ የደቡብ አጋማሽ የአገሪቱ ክፍሎች ለሚካሂዱ የእንስሳት ልማትም ሆነ ለሰብሎችና ለቋሚ ተክሎች የውኃ ፍላጎት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር በመግለጫው ተገልጿል። 

በዚሁ ጊዜ በሰሜን ምስራቅ፣ በመካከለኛውና በምስራቁ የአገሪቱ ክፍሎች ላይ አነስተኛ መጠን ያለው እርጥበት እንደሚጠበቅም ትንበያው አመላክቷል። 

የሚገኘው እርጥበት ለቋሚ ተክሎች የውሃ ፍላጎት ለማሟላት፣ ለአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር  አካባቢዎች የግጦሽ ሳርና የመጠጥ ውኃ አቅርቦትን ለማሻሻልም ጠቀሜታ እንደሚኖረው እንዲሁ። 

መካከለኛው ኦሞ ጊቤ፣ በስምጥ ሸለቆ፣ በጥቂት የላይኛውና የመካከለኛው አባይ፣ በጥቂት የላይኛው ገናሌ ዳዋ መጠነኛ እርጥበት እንደሚያገኙም የአየር ትንበያው ያመላክታል ተብሏል። 

ባሮ አኮቦ፣ ጥቂት የአፋርና ደናክልና የላይኛውና መካከለኛው ተከዜን ጨምሮ መካከለኛው አዋሽ ተፋሰሶችም እንዲሁ መጠነኛ እርጥበት የሚያገኙ አካባቢዎች መሆናቸውም እንዲሁ።

በተጨማሪም የበልግ ወቅትን ቀድመው ለሚጀምሩ አካባቢዎች ማሳን አስቀድሞ ለማዘጋጀት ጠቀሜታ እንደሚኖረው ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል። 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም