ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ስምምነት ቀጠናዊ የኢኮኖሚ ትብብር ይፈጥራል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ስምምነት ቀጠናዊ የኢኮኖሚ ትብብር ይፈጥራል

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 24/2016 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ሥምምነት የሁለቱን ሀገራት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እንደሚያረጋግጥና ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትብብር እንደሚፈጥር ተገለጸ፡፡
የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የተፈራረመችውን በርበራ ወደብን ለረዥም ጊዜ መጠቀም የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ በተመለከተ ለገንዘብ ሚኒስቴርና ለተጠሪ ተቋማት አመራሮችና ሰራተኞች ገለጻ አድርገዋል።
ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት ስምምነቱ ኢትዮጵያ እና ሶማሌላንድ በጋራ እንዲለሙ ከማድረጉም በላይ በቀጣናው ሀገራት መካከል ኢኮኖሚያዊ ትብብር በመፍጠር የላቀ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ከሌሎች ጎረቤት አገራት ጋር የጀመረችው ኢኮኖሚያዊ ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እያደገ የሚሄድ በመሆኑ ይህን ግዙፍ ኢኮኖሚ የሚያስተናግድ የወደብና የሎጂስቲክ ግንኙነት ከጅቡቲ፣ ከኬንያና ከሌሎችም አገራት ጋር እንደሚቀጥል እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ትስስሩና ትብብሩ እየዳበረ እንደሚሄድም አረጋግጠዋል።
የመግባቢያ ስምምነቱ በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ ተመስርቶ ዝርዝር አፈጻጸሙ በሚቀጥለው አንድ ወር ተግባራዊ እንደሚደረግ ጠቅሰዋል።
ስምምነቱ በአጠቃላይ ለባህር ያለንን ተደራሽነት በማሳደግ፣ በኤደን ሰርጥ የሚኖረንን ተሳትፎ በመጨመር፤ የወል እውነትን እና ትርክትን በማሳደግ ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
ከቀጣናዊ ትስስር እና የመሰረተ-ልማት ዝርጋታ አንጻርም ለወደቡ ተደራሽነት የሚሰሩ ስራዎች ትልቅ መነቃቃትን እንደሚፈጥሩ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ(ዶ/ር) በበኩላቸው የዜጎች የዘመናት ቁጭት የሆነው የወደብ ጉዳይ ይህን በመሰለ ሰላማዊ መንገድ እውን በመሆኑ እንኳን ደስ ያለን ብለዋል።
በህጋዊ መንገድ የወደብ ባለቤትና ተጠቃሚ መሆናችን ኢኮኖሚያዊ ብቻ ሳይሆን ሁለንተናዊ ጥቅም ያለው በመሆኑ ታላቅ ሀገራዊ ድል ነው ሲሉ መናገራቸውን ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።