ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት ከሶማሌ ላንድ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ሥምምነት የኢትዮጵያን የንግድ ትስስር ያጠናክራል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት ከሶማሌ ላንድ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ሥምምነት የኢትዮጵያን የንግድ ትስስር ያጠናክራል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 24/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት ከሶማሌ ላንድ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ሥምምነት ኢትዮጵያን በዓለም ገበያ ውስጥ ያላትን የንግድ ትስስር የሚያጠናክር መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገለጸ።
ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት የሚያስችላትን የመግባቢያ ሥምምነት ከሶማሌላንድ ጋር ባሳለፊነው ሰኞ ተፈራርማለች።
የመግባቢያ ሥምምነቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ ፈርመውታል።
በሥምምነቱ መሠረት ኢትዮጵያ ወደብና የጦር ሰፈር ለመገንባት የሚያስችላትን ቦታ በሊዝ የምታገኝ ሲሆን ሶማሌላንድ ደግሞ ከኢትዮጵያ የልማት ኩባንያዎች ድርሻ እንደምታገኝ ተመላክቷል።
የመግባቢያ ሥምምነቱን ተከትሎ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ አቶ ገብረመስቀል ጫላ ለሚኒስቴሩ ሠራተኞችና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመልዕክታቸው የባህር በር አለመኖር በአገሪቱ የገቢና የወጪ ንግድን እንዲሁም አገሪቱ በዓለምና በቀጣናዊ የንግድ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ጫና ሲያሳድር መቆየቱን አስታውሰዋል።
አሁን ላይ የባህር በር ለማግኘት ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ሥምምነት ይህን ችግር የሚቀርፍና የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ ንግድ ተሳትፎ ያጠናክራል ብለዋል።
ይህም አገራዊ የንግድ መጠንና አጠቃላይ የኢኮኖሚ እድገት ላይ አዎንታዊ አስተዋጽዖ እንደሚኖረውም ገልጸው ይህ ውጥን እውን እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋጽዖ ላደረጉት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ( ዶ/ር) ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ በበኩላቸው፤ የመግባቢያ ሥምምነቱ የወጪና የገቢ ንግድን በማቀላጠፍ ረገድ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።
ይህም አገሪቱ ያላትን አቅም አሟጣ በመጠቀም የበለጠ በመሥራትና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በዓለም ዓቀፍ ገበያ ላይ ያላትን ተሳትፎ ለማጠናከር ያስችላታል ነው ያሉት።
ሥምምነቱ ወደ ትግበራ ሲገባ የዋጋ ንረትን በማረጋጋት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ያሉት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፍሰሃ ይታገሱ ናቸው።